መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22


ምዕራፍ 13

እነሆም፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፤ ኢዮርብዓምም ዕጣን እያጠነ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ነበር።
2 ፤ በመሠዊያውም ላይ። መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፥ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ።
3 ፤ በዚያም ቀን። እግዚአብሔር የተናገረው ምልክት ይህ ነው፤ እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፥ በላዩም ያለው አመድ ይፈስሳል ብሎ ምልክት ሰጠ።
4 ፤ ንጉሡም የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የጮኸውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ኢዮርብዓም እጁን ከመሠዊያው አንሥቶ። ያዙት አለ። በእርሱም ላይ የዘረጋት እጅ ደረቀች፥ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም።
5 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፥ አመዱም ከመሠዊያው ፈሰሰ።
6 ፤ ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው። አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፥ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፥ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እንደ ቀድሞም ሆነች።
7 ፤ ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው። ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና እንጀራም ብላ፥ በረከትም እሰጥሃለሁ አለው።
8 ፤ የእግዚአብሔርም ሰው ንጉሡን። የቤትህን እኩሌታ እንኳ ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር አልገባም፥ በዚህም ስፍራ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፤
9 ፤ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ታዝዤአለሁና አለው።
10 ፤ በሌላም መንገድ ሄደ፥ ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ አልተመለሰም።
11 ፤ በቤቴልም አንድ ሽማግሌ ነቢይ ይቀመጥ ነበር፤ ልጆቹም ወደ እርሱ መጥተው በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ያደረገውን ሥራ ሁሉ ነገሩት ደግሞም ለንጉሡ የተናገረውን ቃል ሁሉ ለአባታቸው ነገሩት።
12 ፤ አባታቸውም። በማናቸው መንገድ ሄደ? አላቸው። ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ አመለከቱት።
13 ፤ ልጆቹንም። አህያውን ጫኑልኝ አላቸው፤ አህያውንም በጫኑለት ጊዜ ተቀመጠበት።
14 ፤ ከእግዚአብሔርም ሰው በኋላ ሄደ፤ በአድባርም ዛፍ በታች ተቀምጦ አገኘውና። ከይሁዳ የመጣህ የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ነኝ አለ።
15 ፤ እርሱም። ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፥ እንጀራም ብላ አለው።
16 ፤ እርሱም። ከአንተ ጋር እመለስና እገባ ዘንድ አይቻለኝም፤ በዚህም ስፍራ ከአንተ ጋር እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፤
17 ፤ በዚያ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ተብሎልኛልና አለ።
18 ፤ እርሱም። እኔ ደግሞ እንደ አንተ ነቢይ ነኝ፤ መልአክም። እንጀራ ይበላ ዘንድ ውኃም ይጠጣ ዘንድ ከአንተ ጋር ወደ ቤትህ መልሰው ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ተናገረኝ አለው። ዋሽቶም ተናገረው።
19 ፤ ከእርሱም ጋር ተመለሰ፥ በቤቱም እንጀራ በላ፥ ውኃም ጠጣ።
20 ፤ በማዕድም ተቀምጠው ሳሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ መለሰው ነቢይ መጣ፤
21 ፤ ከይሁዳም ወደ መጣው ወደ እግዚአብሔር ሰው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእግዚአብሔር አፍ ላይ ዐምፀሃልና፥ አምላክህም እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህምና፥
22 ፤ ተመልሰህም። እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ ባለህ ስፍራ እንጀራ በልተሃልና፥ ውኃም ጠጥተሃልና ሬሳህ ወደ አባቶችህ መቃብር አይደርስም ብሎ ጮኸ።
23 ፤ እንጀራም ከበላ፥ ውኃም ከጠጣ በኋላ አህያውን ጫነለት።
24 ፤ ተመልሶም በሄደ ጊዜ በመንገዱ ላይ አንበሳ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋድሞ ነበር፥ አህያውም በእርሱ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ አንበሳውም ደግሞ በሬሳው አጠገብ ቆሞ ነበር።
25 ፤ እነሆም፥ መንገድ አላፊ ሰዎች ሬሳው በመንገዱ ወድቆ አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆሞ አዩ መጥተውም ሽማግሌው ነቢይ ተቀምጦባት በነበረው ከተማ አወሩ።
26 ፤ ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ያን በሰማ ጊዜ። በእግዚአብሔር አፍ ላይ ያመፀ ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ቃል፥ እግዚአብሔር ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ሰብሮም ገድሎታል አለ።
27 ፤ ልጆቹንም። አህያ ጫኑልኝ አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት።
28 ፤ ሄደም፥ ሬሳውም በመንገድ ወድቆ፥ በሬሳውም አጠገብ አህያውና አንበሳው ቆመው፥ አንበሳው ሬሳውን ሳይበላው፥ አህያውንም ሳይሰብረው አገኘ።
29 ፤ ነቢዩም የእግዚአብሔርን ሰው ሬሳ አነሣ፥ በአህያውም ላይ ጭኖ መለሰው፤ ያለቅስለትና ይቀብረው ዘንድ ወደ ገዛ ከተማው ይዞት መጣ።
30 ፤ ሬሳውንም በገዛ መቃብሩ አኖረው፤ ዋይ ዋይ ወንድሜ ሆይ እያሉ አለቀሱለት።
31 ፤ ከቀበረውም በኋላ ልጆቹን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤
32 ፤ በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ፥ በሰማርያም ከተሞች ውስጥ ባሉ በኮረብታዎቹ መስገጃዎች ላይ በእግዚአብሔር ቃል የጮኸው ነገር በእውነት ይደርሳልና።
33 ፤ ከዚህም በኋላ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገድ አልተመለሰም፥ ነገር ግን ለኮረብታዎቹ መስገጃዎች አብልጦ ከሕዝብ ሁሉ ካህናትን አደረገ፤ የሚወድደውንም ሁሉ ይቀድስ ነበር፥ እርሱም ለኮርብታዎቹ መስገጃዎች ካህን ይሆን ነበር።
34 ፤ እስኪፈርስም ከምድርም እስኪጠፋ ድረስ ይህ ነገር ለኢዮርብዓም ቤት ኃጢአት ሆነ።