መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25


ምዕራፍ 24

በእርሱም ዘመን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነዖር ወጣ፥ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ተገዛለት፤ ከዚያም በኋላ ዘወር አለና ዐመፀበት።
2 ፤ እግዚአብሔርም የከለዳውያንንና የሶርያውያንን የሞዓባውያንንም የአሞንንም ልጆች አደጋ ጣዮች ሰደደበት፤ በባሪያዎቹ በነቢያት እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ያጠፉት ዘንድ በይሁዳ ላይ ሰደዳቸው።
3 ፤ ምናሴ ስላደረገው ኃጢአት ሁሉ ስላፈሰሰውም ንጹሕ ደም፥ ኢየሩሳሌምንም በንጹሕ ደም ስለሞላ ከፊቱ ያስወግዳቸው ዘንድ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ትእዛዝ በይሁዳ ላይ ሆነ፤
4 ፤ እግዚአብሔርም ይራራ ዘንድ አልወደደም።
5 ፤ የቀረውም የኢዮአቄም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
6 ፤ ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዮአኪን፤ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
7 ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ለግብጽ ንጉሥ የነበረውን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ወስዶ ነበርና የግብጽ ንጉሥ ከዚያ ወዲያ ከአገሩ አልወጣም።
8 ፤ ዮአኪን መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስምንት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ፤ እናቱም ኔስታ ትባል ነበር፤ እርስዋም የኢየሩሳሌም ሰው የኤልናታን ልጅ ነበረች።
9 ፤ አባቱም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
10 ፤ በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነዖር ባሪያዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፥ ከተማይቱም ተከበበች።
11 ፤ ባሪያዎቹም በከበቡአት ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናብከደነዖር ወደ ከተማይቱ ወጣ።
12 ፤ የይሁዳም ንጉሥ ዮአኮንና እናቱ፥ ባርያዎቹም፥ አለቆቹም፥ ጃንደረቦቹም ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወጡ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ያዘው።
13 ፤ የእግዚአብሔርም ቤት መዛግብትን ሁሉ የንጉሡም ቤት መዛግብትን ከዚያ አወጣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር መቅደስ የሠራውን የወርቁን ዕቃ ሁሉ ሰባበረ።
14 ፤ ኢየሩሳሌምንም ሁሉ፥ አለቆቹንም ሁሉ፥ ጽኑዓን ኃያላኑንም ሁሉ፥ ጠራቢዎቹንም ሁሉ፥ ብረት ሠራተኞቹን ሁሉ አሥር ሺህ ምርኮኞች አፈለሰ፤ ከድሆች ከአገሩ ሕዝብ በቀር ማንም አልቀረም።
15 ፤ ዮአኮንንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ፤ የንጉሡንም እናት፥ የንጉሡንም ሚስቶች፥ ጃንደረቦቹንም፥ የአገሩንም ታላላቆች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማረከ።
16 ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ብርቱዎቹንና ሰልፍ የሚችሉትን ሁሉ፥ ኃያላኑን ሁሉ ሰባት ሺህ ያህል፥ ጠራቢዎችና ብረት ሠራተኞችም አንድ ሺህ፥ ወደ ባቢሎን ማረከ።
17 ፤ የባቢሎንም ንጉሥ የዮአኪንን አጎት ማታንያን በእርሱ ፋንታ አነገሠ፥ ስሙንም ሴዴቅያስ ብሎ ለወጠው።
18 ፤ ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም አሚጣል የተባለች የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።
19 ፤ ኢዮአቄምም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
20 ፤ ከፊቱ አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ቍጣ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆኖአልና፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።