መጽሐፈ አስቴር።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10


ምዕራፍ 5

በሦስተኛውም ቀን አስቴር ልብሰ መንግሥትዋን ለብሳ በንጉሡ ቤት ትይዩ በንጉሡ ቤት በውስጠኛው ወለል ቆመች፤ ንጉሡም በቤቱ መግቢያ ትይዩ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በንጉሡ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ነበር።
2 ፤ ንጉሡም ንግሥቲቱ አስቴር በወለሉ ላይ ቆማ ባየ ጊዜ በዓይኑ ሞገስ አገኘች፤ ንጉሡም በእጁ የነበረውን የወርቁን ዘንግ ለአስቴር ዘረጋላት፤ አስቴርም ቀርባ የዘንጉን ጫፍ ነካች።
3 ፤ ንጉሡም። ንግሥት አስቴር ሆይ፥ የምትለምኚኝ ምንድር ነው? የምትሺውስ ምንድር ነው? እስከ መንግሥቴ እኵሌታ እንኳ ቢሆን ይሰጥሻል አላት።
4 ፤ አስቴርም። ለንጉሡ መልካም ሆኖ ቢታይ ንጉሡ ወዳዘጋጀሁለት ግብዣ ከሐማ ጋር ዛሬ ይምጣ አለች።
5 ፤ ንጉሡም። አስቴር እንዳለች ይደረግ ዘንድ ሐማን አስቸኵሉት አለ። ንጉሡና ሐማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ።
6 ፤ ንጉሡም በወይኑ ጠጅ ግብዣ ሳለ አስቴርን። የምትሺው ምንድር ነው? ይሰጥሻል፤ ልመናሽስ ምንድር ነው? እስከ መንግሥቴ እኵሌታ እንኳ ቢሆን ይደረግልሻል አላት።
7 ፤ አስቴርም መልሳ። ልመናዬና የምሻው ነገር ይህ ነው፤
8 ፤ በንጉሡ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ልመናዬንም ይፈጽም ዘንድና የምሻውን ያደርግ ዘንድ ንጉሡ ደስ ቢያሰኘው፥ ንጉሡና ሐማ ወደማዘጋጅላቸው ግብዣ ይምጡ፤ እንደ ንጉሡም ነገር ነገ አደርጋለሁ አለች።
9 ፤ በዚያም ቀን ሐማ ደስ ብሎት በልቡም ተደስቶ ወጣ፤ ነገር ግን መርዶክዮስ በንጉሡ በር ያለ መነሣትና ያለ መናወጥ ተቀምጦ ባየ ጊዜ ሐማ በመርዶክዮስ ላይ እጅግ ተቈጣ።
10 ፤ ሐማ ግን ታግሦ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ልኮም ወዳጆቹንና ሚስቱን ዞሳራን አስጠራ።
11 ፤ ሐማም የሀብቱን ክብርና የልጆቹን ብዛት፥ ንጉሡም ያከበረበትን ክብር ሁሉ፥ በንጉሡም አዛውንትና ባሪያዎች ላይ ከፍ ከፍ እንዳደረገው አጫወታቸው።
12 ፤ ሐማም። ንግሥቲቱ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ከእኔ በቀር ከንጉሡ ጋር ማንንም አልጠራችም፤ ደግሞ ነገ ከንጉሡ ጋር ወደ እርስዋ ተጠርቻለሁ።
13 ፤ ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ካየሁ ይህ ሁሉ ለእኔ ምንምን አይጠቅምም አለ።
14 ፤ ሚስቱም ዞሳራና ወዳጆቹ ሁሉ። ቁመቱ አምሳ ክንድ የሆነ ግንድ ይደረግ፥ ነገም መርዶክዮስ ይሰቀልበት ዘንድ ለንጉሡ ተናገር፤ ደስም ብሎህ ከንጉሡ ጋር ወደ ግብዣው ግባ አሉት። ነገራቸውም ሐማን ደስ አሰኘው፥ ግንዱንም አስደረገ።