ትንቢተ ዮናስ

1 2 3 4


ምዕራፍ 4

ይህም ዮናስን ከቶ ደስ አላሰኘውም፥ እርሱም ተቈጣ።
2 ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየና። አቤቱ፥ እለምንሃለሁ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር።
3 ፤ አሁንም፥ አቤቱ፥ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፥ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ አለው።
4 ፤ እግዚአብሔርም። በውኑ ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለ።
5 ፤ ዮናስም ከከተማይቱ ወጣ፥ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ፤ ከተማይቱንም የሚያገኛትን እስኪያይ ድረስ በዚያ ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው በታች ተቀመጠ።
6 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ቅል አዘጋጀ፥ ከጭንቀቱም ታድነው ዘንድ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት፤ ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ አለው።
7 ፤ በነጋው ግን ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘጋጀ፥ እርስዋም ቅሊቱን እስክትደርቅ ድረስ መታቻት።
8 ፤ ፀሐይም በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ትኩስ የምሥራቅ ነፋስ አዘጋጀ ዮናስ እስኪዝል ድረስም ፀሐይ ራሱን መታው፤ ለራሱም ሞትን ፈለገና። ከሕይወት ሞት ይሻለኛል አለ።
9 ፤ እግዚአብሔርም ዮናስን። በውኑ ስለዚች ቅል ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለው። እርሱም። እስከ ሞት ድረስ እቈጣ ዘንድ ይገባኛል አለ።
10 ፤ እግዚአብሔርም። አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል።
11 ፤ እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን? አለው።