ትንቢተ ናሆም

1 2 3


ምዕራፍ 2

የሚቀጠቅጥ በአንተ ላይ ወጥቶአል፤ ምሽግን ጠብቅ፥ መንገድንም ሰልል፤ ወገብህን አጽና፥ ኃይልህንም እጅግ አበርታ።
2 ፤ ዘራፊዎች ዘርፈዋቸዋልና፥ የወይናቸውንም አረግ አጥፍተዋልና እግዚአብሔር የያዕቆብን ክብር እንደ እስራኤል ክብር ይመልሳል።
3 ፤ የኃያላኑ ጋሻ ቀልቶአል፥ ጽኑዓንም ቀይ ልብስ ለብሰዋል። እርሱም በሚያዘጋጅበት ቀን ሰረገሎች እንደ እሳት ይንቦገቦጋሉ፤ የጦሩም ሶመያ ይወዛወዛል።
4 ፤ ሰረገሎች በመንገድ ላይ ይነጕዳሉ፥ አደባባይም ይጋጫሉ፤ መልካቸው እንደ ፋና ነው፥ እንደ መብረቅም ይከንፋሉ።
5 ፤ መሳፍንቱን ያስባል፤ በአረማመዳቸው ይሰናከላሉ፤ ፈጥነው በቅጥርዋ ላይ ይወጣሉ፥ መጠጊያም ተዘጋጀለት።
6 ፤ የወንዞቹም መዝጊያዎች ተከፈቱ፥ የንጉሡ ቤትም ቀለጠች።
7 ፤ ንግሥት ተገለጠች፥ ተማረከችም፥ ሴቶች ባሪያዎችዋም እንደ ርግብ እየጮኹና ደረታቸውን እየመቱ ዋይ ዋይ ይላሉ።
8 ፤ ነነዌ ግን ከዱሮ ዘመን ጀምራ እንደ ተከማቸ ውኃ ነበረች፤ አሁን ግን ይሸሻሉ፤ እነርሱም። ቁሙ፥ ቁሙ ይላሉ፥ ነገር ግን የሚመለስ የለም።
9 ፤ መዝገብዋ መጨረሻ የለውምና፥ የከበረውም የዕቃዋ ሁሉ ብዛት አይቈጠርምና ብሩን በዝብዙ፥ ወርቁንም በዝብዙ።
10 ፤ ባዶና ባድማ ምድረ በዳም ሆናለች፤ ልብ ቀልጦአል፥ ጕልበቶችም ተብረክርከዋል፤ በወገብም ሁሉ ሕማም አለ፥ የሰዎችም ሁሉ ፊት ጠቍሮአል።
11 ፤ የአንበሾችም መደብ፥ የአንበሾችም ደቦል የሚሰማራበት፥ አንበሳውና አንበሳይቱ ግልገሉም ሳይፈሩ የሚሄዱት ስፍራ ወዴት ነው?
12 ፤ አንበሳው ለልጆቹ የሚበቃውን ነጠቀ፥ ለእንስቶቹም ሰበረላቸው ዋሻውን በንጥቂያ፥ መደቡንም በቅሚያ ሞልቶታል።
13 ፤ እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ሰረገሎችዋንም አቃጥዬ አጤሳለሁ፥ ሰይፍም የአንበሳ ደቦሎችሽን ይበላቸዋል፤ ንጥቂያሽንም ከምድር አጠፋለሁ፥ የመልክተኞችሽን ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ አይሰማም።