ምዕራፍ 8

ከተራራም በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።
2 እነሆም፥ ለምጻም ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ እያለ ሰገደለት።
3 እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወዳለሁ፥ ንጻ አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ።
4 ኢየሱስም። ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ አለው።
5 ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥
6 ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል ብሎ ለመነው።
7 ኢየሱስም። እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ አለው።
8 የመቶ አለቃውም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በቤቴ ጣራ ከታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል።
9 እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፥ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም። ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም። ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም። ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል አለው።
10 ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም።
11 እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤
12 የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
13 ኢየሱስም ለመቶ አለቃ። ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ።
14 ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤
15 እጅዋንም ዳሰሰ፥ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው።
16 -
17 በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ። እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።
18 ኢየሱስም ብዙ ሰዎች ሲከቡት አይቶ ወደ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዘ።
19 አንድ ጻፊም ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው።
20 ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው።
21 ከደቀ መዛሙርቱም ሌላው። ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ አለው።
22 ኢየሱስም። ተከተለኝ፥ ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው።
23 ወደ ታንኳም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱ ተከተሉት።
24 እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር።
25 ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉ አስነሡት።
26 እርሱም። እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ።
27 ሰዎቹም። ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ ተደነቁ።
28 ወደ ማዶም ወደ ጌርጋሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፥ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ወጥተው ተገናኙት፤ እነርሱም ሰው በዚያ መንገድ ማለፍ እስኪሳነው ድረስ እጅግ ክፉዎች ነበሩ።
29 እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ።
30 ከእነርሱም ርቆ የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማራ ነበር።
31 አጋንንቱም። ታወጣንስ እንደሆንህ፥ ወደ እሪያው መንጋ ስደደን ብለው ለመኑት። ሂዱ አላቸው።
32 እነርሱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ሄዱና ገቡ፤ እነሆም፥ የእሪያዎቹ መንጋ ሁሉ ከአፋፉ ወደ ባሕር እየተጣደፉ ሮጡ በውኃም ውስጥ ሞቱ።
33 እረኞችም ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ሄደው ነገሩን ሁሉ አጋንንትም በአደሩባቸው የሆነውን አወሩ።
34 እነሆም፥ ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ሊገናኝ ወጣ፥ ባዩትም ጊዜ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት።