ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች

1 2 3 4


ምዕራፍ 3

በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው።
2 ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ።
3 እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና።
4 እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ።
5 በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤
6 ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።
7 ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ።
8 -
9 አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤
10 -
11 እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ።
12 አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ።
13 ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥
14 በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ።
15 እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤
16 ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ።
17 ወንድሞች ሆይ፥ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ፥ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ።
18 ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ።
19 መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው።
20 እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤
21 እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።