መጽሐፈ ሩት

1 2 3 4


ምዕራፍ 1

እንዲህም ሆነ፤ መሳፍንት ይፈርዱ በነበረ ጊዜ በአገሩ ላይ ራብ ሆነ። አንድ ሰውም ከሚስቱና ከሁለቱ ልጆቹ ጋር በሞዓብ ምድር ሊቀመጥ ከቤተ ልሔም ይሁዳ ተነሥቶ ሄደ።
2 ፤ የሰውዮውም ስም አቤሜሌክ፥ የሚስቱም ስም ኑኃሚን፥ የሁለቱም ልጆች ስም መሐሎንና ኬሌዎን ነበረ፤ የቤተ ልሔም ይሁዳም የኤፍራታ ሰዎች ነበሩ። ወደ ሞዓብም ምድር መጡ በዚያም ተቀመጡ።
3 ፤ የኑኃሚንም ባል አቤሜሌክ ሞተ፤ እርስዋና ሁለቱ ልጆችዋ ቀሩ።
4 ፤ እነርሱም ከሞዓባውያን ሴቶች ሚስት አገቡ፤ የአንዲቱ ስም ዖርፋ የሁለተኛይቱም ስም ሩት ነበረ። በዚያም አሥር ዓመት ያህል ተቀመጡ።
5 ፤ መሐሎንና ኬሌዎንም ሁለቱ ሞቱ፤ ሴቲቱም ከሁለቱ ልጆችዋና ከባልዋ ተለይታ ቀረች።
6 ፤ እርስዋም በሞዓብ ምድር ሳለች እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ጐበኘ እንጀራም እንደ ሰጣቸው ስለ ሰማች፥ ከሞዓብ ምድር ልትመለስ ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ተነሣች።
7 ፤ እርስዋም ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ከተቀመጠችበት ስፍራ ወጣች፤ ወደ ይሁዳም ምድር ሊመለሱ በመንገድ ሄዱ።
8 ፤ ኑኃሚንም ምራቶችዋን። ሂዱ፥ ወደ እናቶቻችሁም ቤት ተመለሱ፤ በእኔና በሞቱት እንዳደረጋችሁ፥ እግዚአብሔር ቸርነት ያድርግላችሁ።
9 ፤ እግዚአብሔር በየባላችሁ ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ አለቻቸው። ሳመቻቸውም፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ።
10 ፤ እነርሱም። ከአንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን አሉአት።
11 ፤ ኑኃሚንም አለች። ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፤ ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ባሎቻችሁ የሚሆኑ ልጆች በሆዴ አሉኝን?
12 ፤ ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፤ ባል ለማግባት አርጅቻለሁና ሂዱ፤ ተስፋ አለኝ ብል፥ ዛሬ ሌሊትስ እንኳ ባል ባገባ፥ ወንዶች ልጆችም ብወልድ፥
13 ፤ እነርሱ እስኪያድጉ ድረስ ትቆያላችሁን? ስለ እነርሱስ ባል ማግባት ትተዋላችሁን? ልጆቼ ሆይ፥ እንዲህ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ወጥቶአልና ከእናንተ የተነሣ እጅግ ተመርሬአለሁ።
14 ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንደ ገና አለቀሱ፤ ዖርፋም አማትዋን ሳመች፤ ሩት ግን ተጠጋቻት።
15 ፤ ኑኃሚንም። እነሆ፥ ባልንጀራሽ ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፤ አንቺም ደግሞ ከባልንጀራሽ ጋር ተመለሽ አለቻት።
16 ፤ ሩትም። ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፥ በምታድሪበትም አድራለሁና እንድተውሽ ከአንቺም ዘንድ እንድመለስ አታስቸግሪኝ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤
17 ፤ በምትሞችበትም ስፍራ እሞታለሁ፥ በዚያም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር አንቺንና እኔን አንዳች ቢለየን እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ እንዲሁም ይጨምርብኝ አለች።
18 ፤ ኑኃሚንም ከእርስዋ ጋር ለመሄድ እንደ ቈረጠች ባየች ጊዜ እርስዋን ከመናገር ዝም አለች።
19 ፤ ሁሉቱም እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ሄዱ። ወደ ቤተ ልሔምም በደረሱ ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች ሁሉ ስለ እነርሱ። ይህች ኑኃሚን ናትን? እያሉ ተንጫጩ።
20 ፤ እርስዋም። ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ማራ በሉኝ እንጂ ኑኃሚን አትበሉኝ።
21 ፤ በሙላት ወጣሁ፥ እግዚአብሔርም ወደ ቤቴ ባዶዬን መለሰኝ፤ እግዚአብሔር አዋርዶኛልና፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስጨንቆኛልና ኑኃሚን ለምን ትሉኛላችሁ? አለቻቸው።
22 ፤ ኑኃሚንም ከእርስዋም ጋር ከሞዓብ ምድር የተመለሰችው ሞዓባዊቱ ምራትዋ ሩት ተመለሱ። የገብስም መከር በተጀመረ ጊዜ ወደ ቤተልሔም መጡ።