ምዕራፍ 21

የእስራኤልም ሰዎች። ከእኛ ማንም ሰው ልጁን ለብንያም ልጆች አያጋባ ብለው በምጽጳ ተማምለው ነበር።
2 ፤ ሕዝቡም ወደ ቤቴል መጥተው በዚያ በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ ተቀመጡ፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጽኑ ልቅሶ አለቀሱ።
3 ፤ እነርሱም። አቤቱ፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ መታጣቱ፥ ስለ ምን ይህ በእስራኤል ላይ ሆነ? አሉ።
4 ፤ በነጋውም ሕዝቡ ማልደው ተነሡ፥ በዚያም መሠዊያ ሠሩ፥ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትንም አቀረቡ።
5 ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ስላልወጣ ሰው። እርሱ ፈጽሞ ይገደል ብለው ታላቅ መሐላ ምለው ነበርና። ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ ጉባኤ ወደ እግዚአብሔር ያልወጣ ማን ነው? አሉ።
6 ፤ የእስራኤልም ልጆች ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ብንያም ልጆች ተጸጽተው። ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ ጠፍቶአል።
7 ፤ እኛ ልጆቻችንን እንዳንድርላቸው በእግዚአብሔር ምለናልና የተረፉት ሚስቶችን እንዲያገኙ ምን እናድርግ? አሉ።
8 ፤ እነርሱም። ከእስራኤል ነገድ ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ያልወጣ ማን ነው? አሉ። እነሆም፥ ከኢያቢስ ገለዓድ ወደ ሰፈሩ ወደ ጉባኤ ማንም አልወጣም ነበር።
9 ፤ ሕዝቡም በተቈጠሩ ጊዜ፥ እነሆ፥ በኢያቢስ ገለዓድ የሚኖር ሰው አልተገኘም።
10 ፤ ማኅበሩም ወደዚያ አሥራ ሁለት ሺህ ኃያላን ሰዎች ሰድደው። ሂዱ በኢያቢስ ገለዓድም ያሉትን ሰዎች ከሴቶችና ከሕፃናት ጋር በሰይፍ ስለት ግደሉ።
11 ፤ የምታደርጉትም ይህ ነው፤ ወንዱን ሁሉ፥ ከወንድ ጋር የተኛችይቱንም ሴት ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ ብለው አዘዙአቸው።
12 ፤ ወንድ ያላወቁ አራት መቶ ቈነጃጅት ደናግሎች በኢያቢስ ገለዓድ በሚኖሩ መካከል አገኙ፤ በከነዓንም አገር ወዳለችው ወደ ሴሎ ወደ ሰፈሩ አመጡአቸው።
13 ፤ ማኅበሩም ሁሉ በሬሞን ዓለት ወዳሉት ወደ ብንያም ልጆች መልክተኞችን ላኩ፥ በዕርቅ ቃልም ተናገሩአቸው።
14 ፤ በዚያም ጊዜ የብንያም ልጆች ተመለሱ፤ ከኢያቢስ ገለዓድም ሴቶች ያዳኑአቸውን ሴቶች አገቡአቸው። ነገር ግን የሚበቁ ሴቶች አላገኙም።
15 ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ነገድ ውስጥ ስብራት ስላደረገ ሕዝቡ ስለ ብንያም ተጸጸቱ።
16 ፤ የማኅበሩ ሽማግሌዎች። ከብንያም ሴቶች ጠፍተዋልና የቀሩት ሰዎች ሚስት እንዲያገኙ ምን እናደርጋለን? አሉ።
17 ፤ ደግሞም። ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዳይደመሰስ ከብንያም ላመለጡት ርስት ይኑር።
18 ፤ የእስራኤልም ልጆች። ልጁን ለብንያም የሚድር ርጉም ይሁን ብለው ምለዋልና እኛ ልጆቻችንን ለእነርሱ ማጋባት አይሆንልንም አሉ።
19 ፤ እነርሱም። እነሆ፥ በቤቴል በሰሜን በኩል፥ ከቤቴልም ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ በምሥራቅ በኩል፥ በለቦና በደቡብ በኩል ባለችው በሴሎ የእግዚአብሔር በዓል በየዓመቱ አለ አሉ።
20 ፤ የብንያምንም ልጆች እንዲህ ብለው አዘዙአቸው። ሂዱ በወይኑ ስፍራ ተደበቁ፤
21 ፤ ተመልከቱም፥ እነሆም፥ የሴሎ ሴቶች ልጆች አታሞ ይዘው ለዘፈን ሲወጡ ከወይኑ ስፍራ ውጡ፥ ከሴሎም ሴቶች ልጆች ለየራሳችሁ ሚስት ንጠቁ፥ ወደ ብንያም ምድርም ሂዱ።
22 ፤ አባቶቻቸውና ወንድሞቻቸውም ሊጣሉአችሁ ወደ እኛ በመጡ ጊዜ። ስለ እኛ ማሩአቸው፤ እኛ ሚስት ለያንዳንዳቸው በሰልፍ አልወሰድንላቸውምና፥ እናንተም በደል ይሆንባችሁ ስለ ነበረ አላጋባችኋቸውምና፥ እንላችኋለን።
23 ፤ የብንያምም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ በቍጥራቸውም መጠን ከተነጠቁት ዘፋኞች ሚስት ወሰዱ፤ ወደ ርስታቸውም ተመልሰው ሄዱ፥ ከተሞችንም ሠርተው ተቀመጡባቸው።
24 ፤ በዚያን ጊዜም የእስራኤል ልጆች ከዚያ ተነሡ፥ እያንዳንዱም ወደ ነገዱና ወደ ወገኑ ሄደ፤ ሰውም ሁሉ ከዚያ ወደ ርስቱ ተመለሰ።
25 ፤ በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።