ሰቆቃው ኤርምያስ

1 2 3 4 5


ምዕራፍ 5

አቤቱ፥ የሆነብንን አስብ፤ ተመልከት ስድባችንንም እይ።
2 ፤ ርስታችን ለእንግዶች፥ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ።
3 ፤ ድሀ አደጎችና አባት የሌለን ሆነናል፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል።
4 ፤ ውኃችንን በብር ጠጣን እንጨታችንን በዋጋ ገዛን።
5 ፤ አሳዳጆቻችን በአንገታችን ላይ ናቸው፤ እኛ ደክመናል ዕረፍትም የለንም።
6 ፤ ለግብጻውያንና ለአሦራውያን እንጀራ እንጠግብ ዘንድ እጅ ሰጠን።
7 ፤ አባቶቻችን ኃጢአትን ሠሩ ዛሬም የሉም፤ እኛም በደላቸውን ተሸከምን።
8 ፤ ባሪያዎች ሠልጥነውብናል፤ ከእጃቸው የሚታደገን የለም።
9 ፤ ከምድረ በዳ ሰይፍ የተነሣ በሕይወታችን እንጀራችንን እናመጣለን።
10 ፤ ከሚያቃጥል ከራብ ትኩሳት የተነሣ ቁርበታችን እንደ ምድጃ ጠቈረ።
11 ፤ በጽዮን ሴቶችን፥ በይሁዳም ከተሞች ደናግልን አጐሰቈሉ።
12 ፤ አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፤ የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም።
13 ፤ ጕልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፥ ልጆችም ከእንጨት በታች ተሰናከሉ።
14 ፤ ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጕልማሶች ከበገናቸው ተሻሩ።
15 ፤ የልባችን ደስታ ቀርቶአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል።
16 ፤ አክሊል ከራሳችን ወድቆአል፤ ኃጢአት ሠርተናልና ወዮልን!
17 ፤ ስለዚህ ልባችን ታምሞአል፤ ስለዚህም ነገር ዓይናችን ፈዝዞአል፤
18 ፤ ስለ ጽዮን ተራራ፥ ባድማ ሆናለችና፥ ቀበሮችም ተመላልሰውባታልና።
19 ፤ አቤቱ፥ አንተ ለዘላለም ትኖራለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው።
20 ፤ ስለ ምን ለዘላለም ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናለህ?
21 ፤ አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ።
22 ፤ ነገር ግን ፈጽመህ ጥለኸናል፤ እጅግ ተቈጥተኸናል።