ምዕራፍ 1

በሠላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፈቱ፥ የእግዚአብሔርንም ራእይ አየሁ።
2 ፤ ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት
3 ፤ ከወሩም በአምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በከለዳውያን አገር በኮቦር ወንዝ ወደ ቡዝ ልጅ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ። የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ በእኔ ላይ ሆነች፥
4 ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና የሚበርቅም እሳት መጣ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፥ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ እንደሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ ነበረ።
5 ፤ ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር።
6 ፤ ለእያዳንዱም አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት።
7 ፤ እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፤ የእግራቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፤ እንደ ተወለወለ ናስም ይብለጨለጭ ነበር።
8 ፤ በክንፎቻቸውም በታች በእያራቱ ጐድናቸው እንደ ሰው እጅ ነበረ፤ ለአራቱም እንደዚህ ያሉ ፊትና ክንፍ ነበሩአቸው።
9 ፤ ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ የተያያዘ ነበረ፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር፥ እያንዳንዱም ፊቱን አቅንቶ ይሄድ ነበር።
10 ፤ የፊታቸው አምሳያ እንደ ሰው ፊት ነበረ፥ ለአራቱም በስተ ቀኛቸው እንደ አንበሳ ፊት፥ በስተ ግራቸውም እንደ ላም ፊት ነበራቸው፥ ለአራቱም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው።
11 ፤ ክንፋቸውም በላይ ተዘርግቶ ነበር፥ የእያንዳንዱም ሁለት ሁለት ክንፋቸው የተያያዙ ነበሩ፥ ሁለት ሁለቱም ገላቸውን ይከድኑ ነበር።
12 ፤ እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፤ መንፈስም ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር።
13 ፤ በእንስሶቹ መካከል እንደሚነድድ የእሳት ፍም ያለ ምስያ ነበረ፤ በእንስሶች መካከል ወዲህና ወዲያ የሚሄድ እንደ ፋና ያለ ምስያ ነበረ፤ ለእሳቱም ፀዳል ነበረው፥ ከእሳቱም መብረቅ ይወጣ ነበር።
14 ፤ እንስሶቹም እንደ መብረቅ ምስያ ይሮጡና ይመለሱ ነበር።
15 ፤ እንስሶችንም ስመለከት፥ እነሆ፥ በአራቱ እንስሶች አጠገብ በምድር ላይ አንድ አንድ መንኰራኵር አየሁ።
16 ፤ የመንኰራኵሩም መልክ እንደ ቢረሌ ነበረ፤ አራቱም አንድ አምሳያ ነበሩ፤ ሥራቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበረ።
17 ፤ በእያራቱ ጐድናቸው ይሄዱ ነበር፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር።
18 ፤ ቁመታቸውም የረዘመና የሚያስፈራ ነበረ፤ የአራቱም ክበብ ዙሪያው በዓይን ተሞልቶ ነበር።
19 ፤ እንስሶቹም በሄዱ ጊዜ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ሄዱ። እንስሶቹም ከምድር ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ መንኰራኵሮቹ ከፍ ከፍ አሉ።
20 ፤ መንፈሱ ወደሚሄድበት ሁሉ እነርሱ ሄዱ፤ የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና መንኰራኵሮቹ በእነርሱ አጠገብ ከፍ ከፍ አሉ።
21 ፤ የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና እነዚያ ሲሄዱ እነዚህ ይሄዱ ነበር፤ እነዚያም ሲቆሙ እነዚህ ይቆሙ ነበር፤ እነዚያም ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር።
22 ፤ ከእንስሶች ራስ በላይ የሚያስፈራ በረዶ የሚመስል የጠፈር አምሳያ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር።
23 ፤ ከጠፈሩም በታች ክንፎቻቸው እርስ በርሳቸው ተቃንተው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ገላውን የሚከድኑ ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሩት።
24 ፤ ሲሄዱም የክንፎቻቸው ድምፅ እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ፥ እንደ ሁሉን የሚችል የአምላክም ድምፅ፥ እንደ ታላቅም ሠራዊት ድምፅ ሆኖ ሰማሁ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።
25 ፤ በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።
26 ፤ በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ።
27 ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት ምስያ አየሁ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ።
28 ፤ በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።