ትንቢተ ዳንኤል

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 10

በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመት ብልጣሶር ለተባለው ለዳንኤል ነገር ተገለጠለት፤ ነገሩም እውነት ነበረ፥ እርሱም ታላቅ ጦርነት ነው፤ ነገሩንም አስተዋለ፥ በራእዩም ውስጥ ማስተዋል ተሰጠው።
2 ፤ በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ።
3 ፤ ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም።
4 ፤ ከመጀመሪያውም ወር በሀያ አራተኛው ቀን ጤግሮስ በተባለው በታላቁ ወንዝ አጠገብ ሳለሁ፥ ዓይኔን አነሣሁ፥
5 ፤ እነሆም፥ በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ።
6 ፤ አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፥ ፊቱም እንደ መብረቅ ምስያ ነበረ፥ ዓይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፥ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ።
7 ፤ እኔም ዳንኤል ብቻዬን ራእዩን አየሁ፥ ከእኔ ጋር የነበሩ ሰዎች ግን ራእዩን አላዩም፤ ነገር ግን ጽኑ መንቀጥቀጥ ወደቀባቸው፥ ሊሸሸጉም ሸሹ።
8 ፤ እኔም ብቻዬን ቀረሁ ይህንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኃይልም አልቀረልኝም፥ ደም ግባቴም ወደ ማሸብሸብ ተለወጠብኝ፥ ኃይልም አጣሁ።
9 ፤ የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ።
10 ፤ እነሆም፥ አንዲት እጅ ዳሰሰችኝ፥ በጕልበቴና በእጄም አቆመችኝ።
11 ፤ እርሱም። እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ፥ እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፥ ቀጥ ብለህም ቁም አለኝ። ይህንም ቃል ባለኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ።
12 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፤ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ።
13 ፤ የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ እነሆም፥ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት።
14 ፤ ራእዩም ገና ለብዙ ዘመን ነውና በኋለኛው ዘመን ለሕዝብህ የሚሆነውን አስታውቅህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ።
15 ፤ ይህንም ቃል በተናገረኝ ጊዜ ፊቴን ወደ ምድር አቀረቀርሁ፥ ዲዳም ሆንሁ።
16 ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሬን ዳሰሰኝ፤ የዚያን ጊዜም አፌን ከፍቼ ተናገርሁ በፊቴም ቆሞ የነበረውን። ጌታዬ ሆይ፥ ከራእዩ የተነሣ ሕመሜ መጣብኝ፥ ኃይልም አጣሁ።
17 ፤ ይህ የጌታዬ ባሪያ ከዚህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ እንዴት ይችላል? አሁንም ኃይል አጣሁ፥ እስትንፋስም አልቀረልኝም አልሁት።
18 ፤ ደግሞ ሰው የሚመስል ዳሰሰኝ፥ አበረታኝም።
19 ፤ እርሱም። እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፥ አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ በርታ፥ ጽና አለኝ። በተናገረኝም ጊዜ በረታሁና። አበርትተኸኛልና ጌታዬ ይናገር አልሁ።
20 ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። ወደ አንተ የመጣሁት ስለ ምን እንደ ሆነ፥ ታውቃለህን? አሁንም ከፋርስ አለቃ ጋር እዋጋ ዘንድ እመለሳለሁ፤ እኔም ስወጣ፥ እነሆ፤ የግሪክ አለቃ ይመጣል።
21 ፤ ነገር ግን በእውነት ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር ማንም የሚያጸናኝ የለም።