ትንቢተ ዳንኤል

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 4

ከንጉሡ ከናቡከደነፆር በምድር ሁሉ ወደሚቀመጡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም ወደሚናገሩ ሁሉ፥ ሰላም ይብዛላችሁ።
2 ፤ ልዑል አምላክ በፊቴ ያደረገውን ተአምራቱንና ድንቁን አሳያችሁ ዘንድ ወድጃለሁ።
3 ፤ ተአምራቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁም እንዴት ጽኑ ነው! መንግሥቱም የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቱም ለልጅ ልጅ ነው።
4 ፤ እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ በአዳራሼም ተመችቶኝ ነበር።
5 ሕልም አለምሁ፤ እርስዋም አስፈራችኝ፤ በአልጋዬም ላይ የነበረው አሳቤና የራሴ ራእይ አስጨነቁኝ።
6 ስለዚህ የሕልሙን ፍቺ እንዲያስታውቁኝ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ ይገቡ ዘንድ አዘዝሁ።
7 የዚያን ጊዜም የሕልም ተርጓሚዎቹና አስማተኞቹ ከለዳውያኑና ቃላተኞቹ ገቡ፤ ሕልሙንም በፊታቸው ተናገርሁ፥ ፍቺውን ግን አላስታወቁኝም።
8 በመጨረሻም የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር የሚባለው ዳንኤል በፊቴ ገባ፤ እኔም ሕልሙን ነገርሁት እንዲህም አልሁት።
9 የሕልም ተርጓሚዎች አለቃ ብልጣሶር ሆይ፥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለ፥ ከምሥጢርም ሁሉ የሚያስቸግርህ እንደሌለ አውቄአለሁና ያለምሁትን የሕልሜን ራእይ ፍቺውንም ንገረኝ።
10 የራሴ ራእይ በአልጋዬ ላይ ይህ ነበረ፤ እነሆ፥ በምድር መካከል ዛፍ አየሁ፥ ቁመቱም እጅግ ረጅም ነበረ።
11 ዛፉም ትልቅ ሆነ፥ በረታም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ ደረሰ፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ድረስ ታየ።
12 ቅጠሉም። የተዋበ ነበረ ፍሬውም ብዙ ነበረ፥ ለሁሉም መብል ነበረበት፤ ከጥላውም በታች የምድር አራዊት ያርፉበት ነበር፥ በቅርንጫፎቹም ውስጥ የሰማይ ወፎች ይቀመጡ ነበር፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ ከእርሱ ይበላ ነበር።
13 በአልጋዬም ላይ በራሴ ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ወረደ።
14 በታላቅ ድምፅም እየጮኸ እንዲህ አለ። ዛፉን ቍረጡ፥ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ፥ ቅጠሎቹንም አራግፉ፥ ፍሬውንም በትኑ፤ አራዊትም ከበታቹ ወፎቹም ከቅርንጫፉ ይሽሹ።
15 ፤ ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፥ በመስክም ውስጥ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ እድል ፈንታውም በምድር ሣር ውስጥ ከአራዊት ጋር ይሁን።
16 ልቡም ከሰው ልብ ይለወጥ፥ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም ይለፉበት።
17 ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለወደደውም እንዲሰጠው፥ ከሰውም የተዋረደውን እንዲሾምበት ሕያዋን ያውቁ ዘንድ ይህ ነገር የጠባቂዎች ትእዛዝ፥ ይህም ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው።
18 ፤ እኔ ንጉሡ ናቡከደነፆር ይህን ሕልም አልሜአለሁ፤ አንተም፥ ብልጣሶር፥ ፍቺውን አስታውቀኝ፥ የመንግሥቴ ጠቢባን ሁሉ ፍቺውን ያስታውቁኝ ዘንድ አይችሉምና፤ ነገር ግን የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ አለና አንተ ትችላለህ።
19 ፤ የዚያን ጊዜ ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል አንድ ሰዓት ያህል አሰበ፥ ልቡም ታወከ። ንጉሡም መልሶ። ብልጣሶር ሆይ፥ ሕልሙና ፍቺው አያስቸግርህ አለው። ብልጣሶርም መልሶ አለ። ጌታዬ ሆይ፥ ሕልሙ ለሚጠሉህ፥ ፍቺውም ለጠላቶችህ ይሁን።
20 ፤ ትልቅ የነበረው የበረታውም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ የደረሰው፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ድረስ የታየው፥
21 ፤ ቅጠሉም አምሮ የነበረው፥ ፍሬውም የበዛው፥ ለሁሉም መብል የነበረበት፤ በበታቹም የምድር አራዊት የተቀመጡ፥ በቅርንጫፎቹም የሰማይ ወፎች ያደሩበት ያየኸው ዛፍ፤
22 ፤ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ታላቅና ብርቱ የሆንህ አንተ ነህ፤ ታላቅነትህ በዝቶአል፥ እስከ ሰማይም ደርሶአል፥ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው።
23 ፤ ንጉሡም ከሰማይ የወረደውንና። ዛፉን ቍረጡ፥ አጥፉትም፤ ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፤ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ በመስክ ውስጥ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ፥ ሰባት ዘመናትም እስኪያልፉበት ድረስ እድል ፈንታው ከምድር አራዊት ጋር ይሁን ያለውን ቅዱስ ጠባቂ ማየቱ፤ ንጉሥ ሆይ፥ ፍቺው ይህ ነው፤
24 ፤ በጌታዬ በንጉሥ ላይ የወረደው የልዑሉ ትእዛዝ ነው፤
25 ፤ ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፥ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ በሰማይም ጠል ትረሰርሳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል።
26 ፤ የዛፉንም ጉቶ ይተዉት ዘንድ ማዘዙ፥ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ ካወቅህ በኋላ መንግሥትህ ይቆይልሃል።
27 ፤ ንጉሥ ሆይ፥ ስለዚህ ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደ ሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፤ ኃጢአትህንም በጽድቅ፥ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር።
28 ፤ ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ።
29 ፤ ከአሥራ ሁለት ወር በኋላ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ይመላለስ ነበር።
30 ፤ ንጉሡም። ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን? ብሎ ተናገረ።
31 ፤ ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰማይ ወደቀና። ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ። መንግሥት ከአንተ ዘንድ አለፈች ተብሎ ለአንተ ተነግሮአል፤
32 ፤ ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል አለው።
33 ፤ በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጕሩም እንደ ንስር፥ ጥፍሩም እንደ ወፎች እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፥ እንደ በሬም ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።
34 ፤ ዘመኑም ከተፈጸመ በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዓይኔን ወደ ሰማይ አነሣሁ፥ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁ፥ ለዘላለምም የሚኖረውን አመሰገንሁ አከበርሁትም፤ ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነውና፥ መንግሥቱም ለልጅ ልጅ ነውና።
35 ፤ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቈጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚከለክላት ወይም። ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም።
36 ፤ በዚያን ጊዜም አእምሮዬ ተመለሰልኝ፥ ለመንግሥቴም ክብር ግርማዬና ውበቴ ወደ እኔ ተመለሰ፤ አማካሪዎቼና መኳንንቶቼም ፈለጉኝ፥ በመንግሥቴም ውስጥ ጸናሁ፥ ብዙም ክብር ተጨመረልኝ።
37 ፤ አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግናለሁ፥ ታላቅም አደርገዋለሁ፥ አከብረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፥ መንገዱም ፍርድ ነውና፥ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና።