ትንቢተ አሞጽ

1 2 3 4 5 6 7 8 9


ምዕራፍ 7

ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ የኋለኛው ሣር በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፤ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ የበቀለ የገቦ ነበረ።
2 ፤ የምድሩንም ሣር በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ።
3 ፤ እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ይህ አይሆንም፥ ይላል እግዚአብሔር።
4 ፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፤ እርስዋም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች።
5 ፤ እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድትተው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ።
6 ፤ እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ይህ ደግሞ አይሆንም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
7 ፤ እንዲህም አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር።
8 ፤ እግዚአብሔርም። አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። ቱንቢ ነው አልሁ። ጌታም። እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም፤
9 ፤ የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ አለ።
10
11 ፤ የቤቴልም ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም ልኮ። አሞጽ። ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፥ እስራኤልም ከአገሩ ተማርኮ ይሄዳል ብሎአልና አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል ዐምፆብሃል፤ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም አለ።
12 ፤ አሜስያስም አሞጽን። ባለ ራእዩ ሆይ፥ ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፥ በዚያም እንጀራን ብላ፥
13 ፤ በዚያም ትንቢትን ተናገር፤ ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ደግሞ ትንቢት አትናገር አለው።
14 ፤ አሞጽም መልሶ አሜስያስን አለው። እኔ ላም ጠባቂና ወርካ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤
15 ፤ እግዚአብሔርም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ እግዚአብሔርም። ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ።
16 ፤ አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ አንተ። በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ ብለሃል፤
17 ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ምድርህም በገመድ ትከፈላለች፤ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፥ እስራኤልም ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።