ትንቢተ አሞጽ

1 2 3 4 5 6 7 8 9


ምዕራፍ 8

ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ እነሆም፥ የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነበረ።
2 ፤ እርሱም። አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነው አልሁት። እግዚአብሔርም አለኝ። ፍጻሜ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መጥቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም።
3 ፤ የመቅደሱ ዝማሬ በዚያ ቀን ዋይታ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የሰዎችም ሬሳ ይበዛል፥ በስፍራውም ሁሉ በዝምታ ይጣላል።
4 ፤ ችጋረኛውን የምትውጡ፥ የአገሩንም ድሀ የምታጠፉ እናንተ ሆይ።
5 ፤ እህልን እንሸጥ ዘንድ መባቻው መቼ ያልፋል? የኢፍ መስፈሪያውንም እያሳነስን፥ ሰቅሉንም እያበዛን፥ በሐሰተኛም ሚዛን እያታለልን፥
6 ፤ ድሀውን በብር ችጋረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ እንገዛ ዘንድ፥ የስንዴውን ግርድ እንሸጥ ዘንድ ስንዴውን እንድንሸምት ሰንበት መቼ ያልፋል? የምትሉ እናንተ ሆይ፥ ይህን ስሙ።
7 ፤ እግዚአብሔር በያዕቆብ ክብር እንዲህ ብሎ ምሎአል። ሥራቸውን ሁሉ ለዘላለም ምንም አልረሳም።
8 ፤ በውኑ ምድሪቱ ስለዚህ ነገር አትናወጥምን? በእርስዋም የሚኖር ሁሉ አያለቅስምን? ሙላዋም እንደ ወንዙ ትነሣለች፤ እንደ ግብጽም ወንዝ ትነሣለች ደግሞም ትወርዳለች።
9 ፤ በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በብርሃንም ቀን ምድሩን አጨልማለሁ።
10 ፤ ዓመት በዓላችሁንም ወደ ልቅሶ፥ ዝማሬአችሁንም ወደ ዋይታ እለውጣለሁ፤ ማቅንም በወገብ ሁሉ፥ ራስ መንጨትንም በሁሉ ላይ አመጣለሁ፤ እንደ አንድያ ልጅም ልቅሶ፥ ፍጻሜውንም እንደ መራራ ቀን አደርገዋለሁ።
11 ፤ እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም።
12 ፤ ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፥ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ለመሻት ይርዋርዋጣሉ፥ አያገኙትምም።
13 ፤ በዚያ ቀን መልካካሞች ደናግል ጐበዛዝትም በጥም ይዝላሉ።
14 ፤ በሰማርያ ኃጢአት የሚምሉና። ዳን ሆይ፥ ሕያው አምላክህን! ደግሞ። ሕያው የቤርሳቤህን መንገድ! ብለው የሚሉ፥ እነርሱ ይወድቃሉ፥ ደግሞም አይነሡም።