ምዕራፍ 21

ከእነርሱም ተለይተን ተነሣን፤ በቀጥታም ሄደን ወደ ቆስ በነገውም ወደ ሩድ ከዚያም ወደ ጳጥራ መጣን፤
2 ወደ ፊንቄም የሚሻገር መርከብ አግኝተን ገባንና ተነሣን።
3 ቆጵሮስንም ባየናት ጊዜ በስተ ግራችን ተውናት ወደ ሶርያም ሄደን ወደ ጢሮስ ደረስን፥ መርከቡ ሸክሙን በዚያ የሚያራግፍ ነበርና።
4 ደቀ መዛሙርትንም ባገኘን ጊዜ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ አሉት።
5 ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፥ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤
6 እርስ በርሳችንም ተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፥ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
7 እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፥ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን።
8 በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፥ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን።
9 ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት።
10 አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ።
11 ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ። እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ። ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል አለ።
12 ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው።
13 ጳውሎስ ግን መልሶ። እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ።
14 ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ። የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን።
15 ከዚህም ቀን በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን።
16 በቂሣርያም ከነበሩ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ደግሞ ከእኛ ጋር መጡ፥ እነርሱም ወደምናድርበት ወደ ቀደመው ደቀ መዝሙር ወደ ቆጵሮሱ ምናሶን ወደሚሉት ቤት መሩን።
17 ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን።
18 በነገውም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ዘንድ ገባ ሽማግሌዎችም ሁሉ መጡ።
19 ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን በእያንዳንዱ ተረከላቸው።
20 እነርሱም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ አሉትም። ወንድም ሆይ፥ በአይሁድ መካከል አምነው የነበሩት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህ፤ ሁላቸውም ለሕግ የሚቀኑ ናቸው።
21 ልጆቻቸውንም እንዳይገርዙ በሥርዓትም እንዳይሄዱ ብለህ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁድ ሁሉ ሙሴን ይክዱ ዘንድ እንድታስተምር ስለ አንተ ነግረዋቸዋል።
22 እንግዲህ ምን ይሁን? የአንተን መምጣት ይሰማሉና ብዙዎች የግድ ሳይሰበሰቡ አይቀሩም።
23 እንግዲህ ይህን የምንልህን አድርግ፤ ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ።
24 እነዚህንም ይዘህ ከእነርሱ ጋር ንጻ፥ ራሳቸውንም እንዲላጩ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ሁሉም ስለ አንተ የተማሩት ከንቱ እንደ ሆነና አንተ ራስህ ደግሞ ሕጉን እየጠበቅህ በሥርዓት እንድትመላለስ ያውቃሉ።
25 አምነው ስለ ነበሩ አሕዛብ ግን ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ነፍሳቸውን እንዲጠብቁ ፈርደን እኛ ጽፈንላቸዋል።
26 በዚያን ጊዜ ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር እየነጻ፥ መንጻታቸውን የሚፈጽሙበትን ቀን አስታውቆ ወደ መቅደስ ገባ። በዚያም ቀን ስለ እያንዳንዳቸው መሥዋዕትን አቀረቡ።
27 -
28 ሰባቱ ቀንም ይፈጸም ዘንድ ሲቀርብ ከእስያ የመጡ አይሁድ በመቅደስ አይተውት ሕዝብን ሁሉ አወኩና። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ እርዱን ሕዝብን ሕግንም ይህንም ስፍራ ሲቃወም ሰውን ሁሉ በየስፍራው የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ጨምሮም የግሪክን ሰዎች ደግሞ ወደ መቅደስ አግብቶ ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል ብለው እየጮኹ እጃቸውን ጫኑበት።
29 በፊት የኤፌሶኑን ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና ጳውሎስም ወደ መቅደስ ያገባው መስሎአቸው ነው።
30 ከተማውም ሁሉ ታወከ ሕዝቡም ሁሉ ተሰበሰቡ ጳውሎስንም ይዘው ከመቅደስ ውጭ ጎተቱት፥ ወዲያውም ደጆች ተዘጉ።
31 ሊገድሉትም ሲፈልጉ። ኢየሩሳሌም ፈጽማ ታወከች የሚል ወሬ ወደ ጭፍራው ሻለቃ ወጣ፤
32 እርሱም ያን ጊዜ ወታደሮችን ከመቶ አለቆች ጋር ይዞ እየሮጠ ወረደባቸው፤ እነርሱም የሻለቃውንና ወታደሮችን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታት ተዉ።
33 በዚያን ጊዜም የሻለቃው ቀርቦ ያዘውና በሁለት ሰንሰለት ይታሰር ዘንድ አዞ ማን እንደ ሆነና ምን እንዳደረገ ጠየቀ።
34 ሕዝቡም እኵሌቶቹ እንዲህ እኵሌቶቹም እንዲያ እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ስለ ጫጫታውም እርግጡን ማወቅ ባልተቻለ ጊዜ፥ ወደ ወታደሮች ሰፈር ይወስዱት ዘንድ አዘዘ።
35 ወደ ደረጃውም በደረሰ ጊዜ ስለ ሕዝቡ ግፊያ ወታደሮች እንዲሸከሙት ሆነ፤
36 ብዙ ሕዝብ። አስወግደው እያሉና እየጮኹ ይከተሉ ነበርና።
37 ወደ ሰፈርም ሊያገቡት በቀረቡ ጊዜ፥ ጳውሎስ የሻለቃውን። አንድ ነገር ብነግርህ ትፈቅዳለህን? አለው። እርሱም። የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን?
38 አንተ ከዚህ ዘመን አስቀድሞ ከነፍሰ ገዳዮቹ አራቱን ሺህ ሰዎች አሸፍተህ ወደ ምድረ በዳ ያወጣህ የግብፅ ሰው አይደለህምን? አለ።
39 ጳውሎስ ግን። እኔስ አይሁዳዊ በኪልቅያ ያለው የጠርሴስ ሰው ሆኜ ስመ ጥር በሆነ ከተማ የምኖር ነኝ፤ ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ አለ።
40 በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ በእጁ ወደ ሕዝቡ ጠቀሰ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እየተናገረ እንዲህ አለ።