ምዕራፍ 24

ከአምስት ቀንም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚሉት ከአንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ እነርሱም ስለ ጳውሎስ ለአገረ ገዡ አመለከቱት።
2 -
3 በተጠራም ጊዜ ጠርጠሉስ ይከሰው ዘንድ ጀመረ እንዲህ እያለ። ክቡር ፊልክስ ሆይ፥ በአንተ በኩል ብዙ ሰላም ስለምናገኝ ለዚህም ሕዝብ በአሳብህ በየነገሩ በየስፍራውም መልካም መሻሻል ስለሚሆንለት፥ በፍጹም ምስጋና እንቀበለዋለን።
4 ነገር ግን እጅግ እንዳላቆይህ በቸርነትህ በአጭሩ ትሰማን ዘንድ እለምንሃለሁ።
5 ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና፤
6 መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፥ እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን።
7 ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ኃይል ከእጃችን ወሰደው፥
8 ከሳሾቹንም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፤ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ።
9 አይሁድም ደግሞ። ይህ ነገር እንዲሁ ነው እያሉ ተስማሙ።
10 ገዡም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ መለሰ እንዲህ ሲል። ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደ ሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤
11 እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከአሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ።
12 ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም።
13 አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም።
14 ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤
15 እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።
16 ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ።
17 ከብዙ ዓመትም በኋላ ለሕዝቤ ምጽዋትና መሥዋዕት አደርግ ዘንድ መጣሁ፤
18 ይህንም ሳደርግ ሳለሁ ሕዝብ ሳይሰበሰብ ሁከትም ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ።
19 ነገር ግን በእኔ ላይ ነገር ያላቸው እንደ ሆነ፥ በፊትህ መጥተው ይከሱኝ ዘንድ የሚገባቸው ከእስያ የመጡ አንዳንድ አይሁድ አሉ።
20 -
21 ወይም በመካከላቸው ቆሜ። ዛሬ ስለ ሙታን መነሣት በፊታችሁ በእኔ ይፈርዱብኛል ብዬ ከጮኽሁት ከዚህ ከአንድ ነገር በቀር፥ በሸንጎ ፊት ቆሜ ሳለሁ በእኔ አንድ ዓመፃ ያገኙ እንደ ሆን እነዚህ ራሳቸው ይናገሩ።
22 ፊልክስ ግን የመንገዱን ነገር አጥብቆ አውቆአልና። የሻለቃው ሉስዮስ በወረደ ጊዜ ነገራችሁን እቆርጣለሁ ብሎ ወደ ፊት አዘገያቸው።
23 የመቶውንም አለቃ ጳውሎስን ሲጠብቅ እንዲያደላለት፥ ከወዳጆቹም ማንም ሲያገለግለው ወይም ወደ እርሱ ሲመጣ እንዳይከለክልበት አዘዘው።
24 ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ አይሁዳዊት ከነበረች ድሩሲላ ከሚሉአት ከሚስቱ ጋር መጥቶ ጳውሎስን አስመጣ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ማመን የሚናገረውን ሰማው።
25 እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኵነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ። አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ ብሎ መለሰለት።
26 ያን ጊዜም ደግሞ እንዲፈታው ጳውሎስ ገንዘብ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ አደረገ፤ ስለዚህ ደግሞ ብዙ ጊዜ እያስመጣ ያነጋግረው ነበር።
27 ሁለት ዓመትም ከሞላ በኋላ ጶርቅዮስ ፊስጦስ በፊልክስ ፈንታ ተተካ። ፊልክስም አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን እንደ ታሰረ ተወው።