ምዕራፍ 11

አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው፤ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል።
2 ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፤ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።
3 ቅኖች ቅንነታቸው ትመራቸዋለች፤ ወስላቶችን ግን ጠማማነታቸው ታጠፋቸዋለች።
4 በቍጣ ቀን ሀብት አትረባም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች።
5 የፍጹም ሰው ጽድቁ መንገዱን ያቀናለታል፤ ኃጥእ ግን በኃጢአቱ ይወድቃል።
6 ቅኖችን ጽድቃቸው ይታደጋቸዋል፤ ወስላቶች ግን በምኞታቸው ይጠመዳሉ።
7 ኀጥእ በሞተ ጊዜ ተስፋው ይቈረጣል፥ የኃያል አለኝታም ይጠፋል።
8 ጻድቅ ከጭንቀት ይድናል፥ ኀጥእም በእርሱ ፋንታ ይመጣል።
9 ዝንጉ ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፤ ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ።
10 በጻድቃን ልማት ከተማ ደስ ይላታል፥ በኀጥኣንም ጥፋት እልል ትላለች።
11 በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤ በኀጥኣን አፍ ግን ትገለበጣለች።
12 ወዳጁን የሚንቅ እርሱ አእምሮ የጐደለው ነው፤ አስተዋይ ግን ዝም ይላል።
13 ለሐሜት የሚሄድ ምሥጢሩን ይገልጣል፤ በመንፈስ የታመነ ግን ነገሩን ይሰውራል።
14 መልካም ምክር ከሌለ ዘንድ ሕዝብ ይወድቃል፤ በመካሮች ብዛት ግን ደኅንነት ይሆናል።
15 ለማያውቅ የሚዋስ ክፉ መከራን ይቀበላል፤ ዋስነትን የሚጠላ ግን ይድናል።
16 ሞገስ ያላት ሴት ክብርን ታገኛለች፥ ሀኬተኖችም ሀብትን ያገኛሉ።
17 ቸር ሰው ለራሱ መልካም ያደርጋል፤ ጨካኝ ግን ሥጋውን ይጐዳል።
18 የኀጥእ ሰው ሞያ ሐሰተኛ ነው፤ ጽድቅን የሚዘራ ግን የታመነ ዋጋ አለው።
19 በጽድቅ የሚጸና በሕይወት ይኖራል፤ ክፋትን የሚከተል ግን ለሞቱ ነው።
20 ልበ ጠማሞች በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊዎች ናቸው፤ በመንገዳቸው ፍጹማን የሆኑ ግን የተወደዱ ናቸው።
21 ክፉ ሰው እጅ በእጅ ሳይቀጣ አይቀርም፤ የጻድቃን ዘር ግን ይድናል።
22 የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደ ሆነ፥ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት።
23 የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነው፤ የኀጥኣን ተስፋ ግን መቅሠፍት ነው።
24 ያለውን የሚበትን ሰው አለ፥ ይጨመርለታልም፤ ያለ ቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ፥ ይደኸያልም።
25 የምትባረክ ነፍስ ትጠግባለች፥ የረካም እርሱ ደግሞ ይረካል።
26 እህልን የሚያስቀር ሰው በሕዝብ ዘንድ ይረገማል፤ በረከት ግን በሚሸጠው ራስ ላይ ነው።
27 መልካምን ተግቶ የሚሻ ደስታን ይፈልጋል፤ ክፉን በሚፈልግ ግን ክፉ ይመጣበታል።
28 በባለጠግነቱ የሚተማመን ሰው ይወድቃል ጻድቃን ግን እንደ ቅጠል ይለመልማሉ።
29 ቤቱን የሚያውክ ሰው ነፋስን ይወርሳል፥ ሰነፍም ለጠቢብ ተገዥ ይሆናል።
30 የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፥ ነፍሶችንም የሚሰበስብ እርሱ ጠቢብ ነው።
31 እነሆ፥ ጻድቅ በምድር ላይ ፍዳውን የሚቀበል ከሆነ፥ ይልቁንስ ኀጥእና ዓመፀኛ እንዴት ይሆናሉ!