ትንቢተ ኢዮኤል

1 2 3


ምዕራፍ 1

ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2 ፤ እናንተ ሽማግሌዎች፥ ይህን ስሙ፤ በምድርም የምትኖሩ ሁሉ፥ አድምጡ። ይህ በዘመናችሁ ወይስ በአባቶቻችሁ ዘመን ሆኖ ነበርን?
3 ፤ ይህን ለልጆቻችሁ ንገሩ፤ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፥ ልጆቻቸውም ለኋለኛው ትውልድ ይንገሩ።
4 ፤ ከተሞች የቀረውን አንበጣ በላው፤ ከአንበጣም የቀረውን ደጎብያ በላው፤ ከደጎብያም የቀረውን ኩብኩባ በላው።
5 ፤ በተሃ ወይን ጠጃችሁ ከአፋችሁ ተወግዶአልና እናንተ ሰካራሞች፥ ነቅታችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የወይን ጠጅ የምትጠጡ ሁሉ፥ ዋይ በሉ።
6 ፤ ቍጥርም የሌለው ብርቱ ሕዝብ በምድሬ ላይ ወጥቶአልና፤ ጥርሳቸው እንደ አንበሳ ጥርስ፥ መንጋጋቸውም እንደ እንስቲቱ አንበሳ መንጋጋ ነው።
7 ፤ ወይኔን ባዶ ምድር አደረገው፥ በለሴንም ሰበረው፤ ባዶም አደረገው፥ ጣለውም፤ ቅርንጫፎቹም ነጡ።
8 ፤ ለቍንጅናዋ ባል ማቅ ለብሳ እንደምታለቅስ ድንግል አልቅሺ።
9 ፤ የእህሉ ቍርባንና የመጠጡ ቍርባን ከእግዚአብሔር ቤት ተወግዶአል፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ካህናቱ አለቀሱ።
10 ፤ እህሉ ጠፍቶአልና፥ ወይኑም ደርቆአልና፥ ዘይቱም ጐድሎአልና እርሻው ምድረ በዳ ሆኖአል፥ ምድሪቱም አልቅሳለች።
11 ፤ መከሩ ከእርሻቸው ጠፍቶአልና ገበሬዎች ስለ ስንዴውና ስለ ገብሱ አፈሩ፤ የወይን አትክልተኞችም አለቀሱ።
12 ፤ ወይኑ ደርቆአል፥ በለሱም ጠውልጎአል፤ ሮማኑና ተምሩ እንኰዩም የምድርም ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፤ ደስታም ከሰው ልጆች ዘንድ ርቆአል።
13 ፤ የእህሉ ቍርባንና የመጠጡ ቍርባን ከአምላካችሁ ቤት ቀርቶአልና እናንተ ካህናት፥ ማቅ ታጥቃችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የመሠዊያ አገልጋዮች፥ ዋይ በሉ፤ እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች፥ ኑ፥ ሌሊቱን ሁሉ በማቅ ላይ ተኙ።
14 ፤ ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሽምግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ።
15 ፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና ለቀኑ ወዮ! እርሱም ሁሉን ከሚችል ከአምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል።
16 ፤ ከዓይናችን ፊት ምግብ፥ ከአምላካችንም ቤት ደስታና እልልታ የጠፋ አይደለምን?
17 ፤ ዘሩ በምድር ውስጥ በሰበሰ፤ እህሉ ደርቆአልና ጎተራዎቹ ባዶ ናቸው፥ ጎታዎቹም ፈርሰዋል።
18 ፤ እንስሶች እጅግ ጮኹ፤ የላምም መንጎች ማሰማርያ የላቸውምና ተጠራጠሩ፤ የበግም መንጎች ጠፍተዋል።
19 ፤ አቤቱ፥ እሳት የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና፥ ነበልባሉም የዱሩን ዛፍ ሁሉ አቃጥሎአልና ወደ አንተ እጮኻለሁ።
20 ፤ ፈሳሹ ውኃ ደርቆአልና፥ እሳቱም የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና የምድር አራዊት ወደ አንተ አለኸለኩ።