ትንቢተ ኢዮኤል

1 2 3


ምዕራፍ 3

እነሆም፥ በዚህ ወራትና በዚህ ዘመን፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ፥
2 ፤ አሕዛብን ሁሉ ሰብስቤ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤ በዚያም ስለ ሕዝቤና ስለ ርስቴ ስለ እስራኤል በአሕዛብ መካከል የበተኑአቸውን ምድሬንም የተካፈሉአትን እፋረድባቸዋለሁ።
3 ፤ በሕዝቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ ወንድ ልጅን ለጋለሞታ ዋጋ ሰጡ፥ ሴት ልጅን ለወይን ጠጅ ሸጡ፥ ጠጡም።
4 ፤ ጢሮስና ሲዶና የፍልስጥኤምም ግዛት ሁሉ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር ለእኔ ምን አለኝ? በውኑ ብድራትን ትመልሱልኛላችሁን? ብድራትን ብትመልሱልኝ ፈጥኜ በችኰላ ብድራታችሁን በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ።
5 ፤ ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋልና፥ የተወደደውንም መልካሙን ዕቃዬን ወደ መቅደሳችሁ አግብታችኋልና፥
6 ፤ ከዳርቻቸውም ታርቁአቸው ዘንድ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ልጆች ለግሪክ ሰዎች ሸጣችኋልና፥
7 ፤ እነሆ፥ እነርሱን ከሸጣችሁበት ስፍራ አስነሣቸዋለሁ፥ ብድራታችሁንም በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ።
8 ፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን በይሁዳ ልጆች እጅ እሸጣለሁ፥ እነርሱም ለሩቆቹ ሕዝብ ለሳባ ሰዎች ይሸጡአችኋል።
9 ፤ ይህን በአሕዛብ መካከል አውጁ ለሰልፍ ተዘጋጁ ኃያላንን አስነሡ ሰልፈኞች ሁሉ ይቅረቡ ይውጡም።
10 ፤ ማረሻችሁን ሰይፍ፥ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ፤ ደካማውም። እኔ ብርቱ ነኛ ይበል።
11 ፤ እናንተ በዙሪያ ያላችሁ አሕዛብ ሁሉ፥ ቸkWlaችሁ ኑ፥ ተሰብሰቡ፤ አቤቱ፥ ኃያላኖችህን ወደዚያ አውርድ።
12 ፤ አሕዛብ ይነሡ፥ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፤ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ በዚያ እቀመጣለሁና።
13 ፤ መከሩ ደርሶአልና ማጭድ ስደዱ መጥመቂያውም ሞልቶአልና ኑ እርገጡ፤ ክፉታቸውም በዝቶአልና መጥመቂያ ሁሉ ፈርሶአል።
14 ፤ የእግዚአብሔር ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቦአልና የብዙ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ።
15 ፤ ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል።
16 ፤ እግዚአብሔርም በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፥ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል።
17 ፤ እኔም በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ የዚያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም።
18 ፤ በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ፥ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ ከእግዚአብሔርም ቤት ምንጭ ትፈልቃለች፥ የሰጢምንም ሸለቆ ታጠጣለች።
19 ፤ በአገራቸው ንጹሑን ደም አፍስሰዋልና በይሁዳ ልጆች ላይ ስላደረጉት ግፍ ግብጽ ምድረ በዳ፥ ኤዶምያስም በረሃ ይሆናል።
20 ፤ ነገር ግን ይሁዳ ለዘላለም፥ ኢየሩሳሌምም ለልጅ ልጅ መኖሪያ ይሆናል።
21 ፤ እኔም ንጹሕ ያላደረግሁትን ደማቸውን ንጹሕ አደርገዋለሁ፥ እግዚአብሔርም በጽዮን ያድራል።