ትንቢተ ኢዮኤል

1 2 3


ምዕራፍ 2

የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና፥ እርሱም ቀርቦአልና በጽዮን መለከትን ንፉ፥ በቅዱሱም ተራራዬ ላይ እሪ በሉ፤ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ፤ የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና፤
2 ፤ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፤ ታላቅና ብርቱ ሕዝብ በተራሮች ላይ እንደ ወገግታ ተዘርግቶአል፤ ከዘላለምም ጀምሮ እንደ እነርሱ ያለ አልነበረም፥ ከእነርሱም በኋላ እስከ ብዙ ትውልድ ድረስ እንደ እነርሱ ያለ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።
3 ፤ እሳት በፊታቸው ትባላለች፥ በኋላቸውም ነበልባል ታቃጥላለች፤ ምድሪቱ በፊታቸው እንደ ዔድን ገነት፥ በኋላቸውም የምድረ በዳ በረሃ ናት፤ ከእነርሱም የሚያመልጥ የለም።
4 ፤ መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፥ እንደ ፈረሶችም ይሮጣሉ።
5 ፤ በተራራ ላይ እንዳሉ ሰረገሎች ድምፅ፥ ገለባውንም እንደሚበላ እንደ እሳት ነበልባል ድምፅ፥ ለሰልፍም እንደ ተዘጋጀ እንደ ብርቱ ሕዝብ ያኰበኵባሉ።
6 ፤ ከፊታቸው አሕዛብ ይንቀጠቀጣሉ፤ የሰውም ፊት ሁሉ ይጠቍራል።
7 ፤ እንደ ኃያላን ይሮጣሉ፥ እንደ ሰልፈኞችም በቅጥሩ ላይ ይወጣሉ፤ እያንዳንዱም በመንገዱ ላይ ይራመዳል፥ ከእርምጃቸውም አያፈገፍጉም።
8 ፤ አንዱ ካንዱ ጋር አይጋፉም፥ እያንዳንዱም መንገዱን ይጠበጥባል፤ በሰልፍ መካከል ያልፋሉ፥ እነርሱም አይቈስሉም።
9 ፤ በከተማም ያኰበkWbaሉ፥ በቅጥሩም ላይ ይሮጣሉ፤ ወደ ቤቶችም ይወጣሉ፥ እንደ ሌባም በመስኮቶች ይገባሉ።
10 ፤ ምድሪቱም ከፊታቸው ትናወጣለች፥ ሰማያትም ይንቀጠቀጣሉ፤ ፀሐይና ጨረቃም ይጨልማሉ፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ይሰውራሉ።
11 ፤ እግዚአብሔርም በሠራዊቱ ፊት ድምፁን ይሰጣል፤ ሰፈሩ እጅግ ብዙ ነውና፥ ቃሉንም የሚያደርግ እርሱ ኃያል ነውና፤ የእግዚአብሔርም ቀን ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ ነውና ማንስ ይችለዋል?
12 ፤ አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ።
13 ፤ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።
14 ፤ የሚመለስና የሚጸጸት እንደ ሆነ፥ ለአምላካችሁም ለእግዚአብሔር የእህልና የመጠጥ ባን የሚሆነውን በረከት የሚያተርፍ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?
15 ፤ በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥
16 ፤ ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፤ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ።
17 ፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዬች ካህናት ከወለሉና ከመሠዊያው መካከል እያለቀሱ። አቤቱ፥ ለሕዝብህ ራራ፥ አሕዛብም እንዳይነቅፉአቸው ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ፤ ከአሕዛብ መካከል። አምላካቸው ወዴት ነው? ስለ ምን ይላሉ? ይበሉ።
18 ፤ እግዚአብሔርም ስለ ምድሩ ቀና፥ ለሕዝቡም ራራለት።
19 ፤ እግዚአብሔርም መልሶ ሕዝቡን። እነሆ፥ እህልንና ወይንን ዘይትንም እሰድድላችኋለሁ፥ እናንተም በእርሱ ትጠግባላችሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ በአሕዛብ መካከል መሰደቢያ አላደርጋችሁም።
20 ፤ የሰሜንንም ሠራዊት ከእናንተ ዘንድ አርቃለሁ፥ ወደ በረሃና ወደ ምድረበዳ፥ ፊቱን ወደ ምሥራቁ ባሕር ጀርባውንም ወደ ምዕራቡ ባሕር አድርጌ አሳድደዋለሁ፤ እርሱም ትዕቢትን አድርጎአልና ግማቱ ይወጣል፥ ክርፋቱም ይነሣል አለ።
21 ፤ ምድር ሆይ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አድርጎአልና አትፍሪ፥ ደስም ይበልሽ፥ እልልም በዪ።
22 ፤ እናንተ የምድር እንስሶች ሆይ፥ የምድር በዳው ማሰማርያ ለምልሞአልና፥ ዛፉም ፍሬውን አፍርቶአልና፥ በለሱና ወይኑም ኃይላቸውን ሰጥተዋልና አትፍሩ።
23 ፤ እናንተ የጽዮን ልጆች፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር የፊተኛውን ዝናብ በጽድቅ ሰጥቶአችኋልና፥ እንደ ቀድሞውም የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ አዝንቦላችኋልና በእርሱ ደስ ይበላችሁ፥ ለእርሱም እልል በሉ።
24 ፤ አውድማዎችም እህልን ይሞላሉ፥ መጥመቂያዎችም የወይን ጠጅንና ዘይትን አትረፍርፈው ያፈስሳሉ።
25 ፤ የሰደድሁባችሁ ታላቁ ሠራዊቴ አንበጣና ደጎብያ ኩብኩባና ተምች የበላቸውን ዓመታት እመልስላችኋለሁ።
26 ፤ ብዙ መብል ትበላላችሁ፥ ትጠግቡማላችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተአምራትን የሠራውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ስም ታመሰግናላችሁ፤ ሕዝቤም ለዘላለም አያፍርም።
27 ፤ እኔም በእስራኤል መካከል እንዳለሁ፥ እኔም አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤ ሕዝቤም ለዘላለም አያፍርም።
28 ፤ ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፥ ጐበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤
29 ፤ ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤
30 ፤ በላይ በሰማይ ድንቆችን አሳያለሁ፥ በታች በምድርም ደምና እሳት የጢስም ጭጋግ።
31 ፤ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል።
32 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ የእግዚአብሔር ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም መድኃኒት ይገኛል። ደግሞም እግዚአብሔር የጠራቸው፥ የምስራች የሚሰበከላቸው ይገኛሉ።