ትንቢተ ሚክያስ

1 2 3 4 5 6 7


ምዕራፍ 4

በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።
2 ፤ ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የእግዚአብሔር ቃል ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው። ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በፍለጋውም እንሄዳለን ይላሉ።
3 ፤ በብዙዎችም አሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች አሕዛብ ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፥ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም።
4 ፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፥ የሚያስፈራውም የለም።
5 ፤ ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፥ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን።
6 ፤ በዚያ ቀን አንካሳይቱን እሰበስባለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የባከነችውንና ያስጨነቅኋትንም አከማቻለሁ፤
7 ፤ አንካሳይቱንም ለቅሬታ፥ ወደ ሩቅም የተጣለችውን ለብርቱ ሕዝብ አደርጋታለሁ፤ ከዚያም ወዲያ እስከ ዘላለም ድረስ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።
8 ፤ አንተም የመንጋ ግንብ ሆይ፥ የጽዮን ሴት ልጅ አምባ፥ ወደ አንተ ትመጣለች፤ የቀደመችው ግዛት፥ የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ መንግሥት ትደርሳለች።
9 ፤ አሁንስ ለምን ትጮኺአለሽ? እንደምትወልድ ሴት ምጥ የደረሰብሽ፥ ንጉሥ ስለሌለሽ ነውን? ወይስ መካሪ ስለ ጠፋብሽ ነውን?
10 ፤ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እንደምትወልድ ሴት አምጠሽ ውለጂ፤ አሁን ከከተማ ትወጫለሽና፥ በሜዳም ትቀመጫለሽ፥ ወደ ባቢሎንም ትደርሻለሽ፤ በዚያም ያድንሻል፥ በዚያም እግዚአብሔር ከጠላቶችሽ እጅ ይቤዥሻል።
11 ፤ አሁንም። ርኩስ ትሁን፥ ዓይናችንም በጽዮን ላይ ይይ የሚሉ ብዙ አሕዛብ በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል።
12 ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን አሳብ አያውቁም፥ ምክሩንም አያስተውሉም፤ እንደ ነዶ ወደ አውድማ አከማችቶአቸዋልና።
13 ፤ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ቀንድሽን ብረት፥ ጥፍርሽንም ናስ አደርጋለሁና ተነሺ አሂጂ፤ ብዙ አሕዛብንም ታደቅቂአለሽ፤ ትርፋቸውንም ለእግዚአብሔር፥ ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ ትቀድሻለሽ።