ትንቢተ ሚክያስ

1 2 3 4 5 6 7


ምዕራፍ 5

የጭፍሮች ሴት ልጅ ሆይ፥ ጭፍሮችሽን አሁን ሰብስቢ፤ ከብቦ አስጨንቆናል፤ የእስራኤልን ፈራጅ ጕንጩን በበትር ይመታሉ።
2 ፤ አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።
3 ፤ ስለዚህ ወላጂቱ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ የቀሩትም ወንድሞቹ ወደ እስራኤል ልጆች ይመለሳሉ።
4 ፤ እርሱም ይቆማል፥ በእግዚአብሔርም ኃይል በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ግርማ መንጋውን ይጠብቃል፤ እነርሱም ይኖራሉ፤ እርሱ አሁን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ይሆናልና።
5 ፤ ይህም ለሰላም ይሆናል፤ አሦራዊውም ወደ አገራችን በገባ ጊዜ፥ ምድራችንንም በረገጠ ጊዜ ሰባት እረኞችና ስምንት አለቆች እናስነሣበታለን።
6 ፤ የአሦርንም አገር በሰይፍ፥ የናምሩድንም አገር በመግቢያው ውስጥ ያፈርሳሉ፤ አሦራዊውም ወደ አገራችን በገባ ጊዜ፥ ዳርቾቻችንንም በረገጠ ጊዜ እርሱ ይታደገናል።
7 ፤ የያዕቆብም ቅሬታ በብዙ አሕዛብ መካከል ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ ጠል፥ በሣር ላይ እንደሚወድ ካፊያ፤ ሰውንም እንደማይጠብቅ፥ የሰውንም ልጆች ተስፋ እንደማያደርግ ይሆናል።
8 ፤ በዱር አራዊትም መካከል እንዳለ አንበሳ፥ በበጎች መንጋም መካከል አልፎ እንደሚረግጥ፥ የሚታደግም ሳይኖር እንደሚነጥቅ እንደ አንበሳ ደቦል፥ እንዲሁ የያዕቆብ ቅሬታ በአሕዛብና በብዙ ወገኖች መካከል ይሆናል።
9 ፤ እጅህ በጠላቶችህ ላይ ከፍ ከፍ ትበል፥ ጠላቶችህም ሁሉ ይጥፉ።
10 ፤ በዚያም ቀን ፈረሶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ሰረገሎችህንም እሰብራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤
11 ፤ የምድርህንም ከተሞች አጠፋለሁ፥ ምሽጎችህንም ሁሉ አፈርሳለሁ፤
12 ፤ መተትንም ከእጅህ አጠፋለሁ፥ ምዋርተኞችም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆኑልህም፤
13 ፤ የተቀረጹትን ምስሎችህንና ሐውልቶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ለእጅህም ሥራ ከእንግዲህ ወዲህ አትሰግድም፤
14 ፤ የማምለኪያ ዐፀዶችህንም ከመካከልህ እነቅላለሁ፥ ከተሞችህንም አፈርሳለሁ።
15 ፤ ባልሰሙም አሕዛብ ላይ በቍጣና በመዓት እበቀላለሁ።