ትንቢተ ሚክያስ

1 2 3 4 5 6 7


ምዕራፍ 7

የዛፍ ፍሬና የወይን ፍሬ ከተለቀሙ በኋላ እንደ ቀረው ቃርሚያ ሆኛለሁና ወዮልኝ! መብል የሚሆን ዘለላ፥ ነፍሴም የተመኘችው በመጀመሪያ የበሰለው በለስ የለም።
2 ፤ ደግ ሰው ከምድር ጠፍቶአል፥ በሰውም መካከል ቅን የለም፤ ሁሉ ደምን ለማፍሰስ ያደባሉ፥ ሰውም ሁሉ ወንድሙን በመረብ ለመያዝ ይከታተለዋል።
3 ፤ እጆቻቸውን ለክፋት ያነሣሉ፤ አለቃውና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል፤ እንዲሁም ክፋትን ይጐነጕናሉ።
4 ፤ ከእነርሱም ሁሉ የተሻለው እርሱ እንደ አሜከላ ነው፥ ከሁሉም ቅን የሆነው እንደ ኵርንችት ነው፤ ጠባቆችህ የሚጐበኙበት ቀን መጥቶአል፤ አሁን ይሸበራሉ።
5 ፤ ባልንጀራን አትመኑ፥ በወዳጅም አትታመኑ፤ የአፍህን ደጅ በብብትህ ከምትተኛው ጠብቅ።
6 ፤ ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃልና፥ ሴት ልጅ በእናትዋ ላይ፥ ምራቲቱም በአማትዋ ላይ ትነሣለችና፥ የሰው ጠላቶች የቤቱ ሰዎች ናቸውና።
7 ፤ እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፥ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አምላኬም ይሰማኛል።
8 ፤ ጠላቴ ሆይ፥ ብወድቅ እነሣለሁና፥ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ።
9 ፤ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁና እስኪምዋገትልኝ ድረስ፥ ፍርድን ለእኔ እስኪያደርግ ድረስ ቍጣውን እታገሣለሁ። ወደ ብርሃን ያወጣኛል፥ ጽድቅንም አያለሁ።
10 ፤ ጠላቴም ታያለች፥ እኔንም። አምላክህ እግዚአብሔር ወዴት ነው? ያለች በእፍረት ትከደናለች።
11 ፤ ዓይኖቼ ይመለከቱአታል፤ አሁን እንደ መንገድ ጭቃ ትረገጣለች። ቅጥርሽ በሚሠራበት በዚያ ቀን ድንበርሽ ትስፋፋለች።
12 ፤ በዚያ ቀን ከአሦርና ከግብጽ ከተሞች፥ ከግብጽ እስከ ወንዙ፥ ከባሕርም እስከ ባሕር፥ ከተራራም እስከ ተራራ ድረስ ወደ አንቺ ይመጣሉ።
13 ፤ ምድሪቱ ግን በሚኖሩባት በሥራቸው ፍሬ ምክንያት ባድማ ትሆናለች።
14 ፤ በቀርሜሎስ መካከል ባለው ዱር ብቻቸውን የተቀመጡት ሰዎችህ፥ የርስትህን በጎች፥ በበትርህ አግድ፤ እንደ ቀደመውም ዘመን በበሳንና በገለዓድ ይሰማሩ።
15 ፤ ከግብጽ ምድር እንደ ወጣህበት ዘመን ተአምራትን አሳያቸዋለሁ።
16 ፤ አሕዛብ አይተው በጕልበታቸው ሁሉ ያፍራሉ፤ እጃቸውን በአፋቸው ላይ ያኖራሉ፥ ጆሮአቸውም ትደነቍራለች፤
17 ፤ እንደ እባብም መሬት ይልሳሉ፥ እንደ ምድርም ተንቀሳቃሾች እየተንቀጠቀጡ ከግንባቸው ይመጣሉ፤ ፈርተውም ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመጣሉ፥ ስለ አንተም ይፈራሉ።
18 ፤ በደልን ይቅር የሚል፥ የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቍጣውን ለዘላለም አይጠብቅም።
19 ፤ ተመልሶ ይምረናል፤ ክፋታችንንም ይጠቀጥቃል፥ ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል።
20 ፤ ከቀድሞ ዘመን ጀምረህ ለአባቶቻችን የማልህላቸውን እውነት ለያዕቆብ፥ ምሕረትንም ለአብርሃም ታደርጋለህ።