መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 16

የዮሴፍም ልጆች ዕጣ በኢያሪኮ አጠገብ በምሥራቁ በኩል ካለው ከዮርዳኖስ አንሥቶ በምድረ በዳውና በተራራማው በኩል ከኢያሪኮ ወደ ቤቴል ወጣ፤
2 ፤ ከቤቴል ወደ ሎዛ ወጣ፥ በአርካውያንም ዳርቻ በኩል ወደ አጣሮት አለፈ፥
3 ፤ ወደ ምዕራብም እስከ የፍሌጣውያን ዳርቻ እስከ ታችኛው ቤትሖሮን ዳርቻ እስከ ጌዝር ድረስ ወረደ፥ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ።
4 ፤ የዮሴፍም ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ርስታቸውን ወረሱ።
5 ፤ የኤፍሬምም ልጆች ድንበር በየወገኖቻቸው እንደዚህ ነበረ፤ በምሥራቅ በኩል የርስታቸው ድንበር አጣሮትአዳር እስከ ላይኛው ቤትሖሮን ድረስ ነበረ፤
6 ፤ ድንበሩም ወደ ምዕራብ ወደ ሚክምታት በሰሜን በኩል ወጣ፤ ድንበሩም ወደ ምሥራቅ ወደ ተአናትሴሎ ዞረ፥ ወደ ኢያኖክ በምሥራቅ በኩል አለፈ፥
7 ፤ ከኢያኖክም ወደ አጣሮትና ወደ ነዓራት ወረደ፤ ወደ ኢያሪኮም ደረሰ፥ ወደ ዮርዳኖስም ወጣ።
8 ፤ ድንበሩም ከታጱዋ ወደ ምዕራብ እስከ ቃና ወንዝ ድረስ አለፈ፥ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። የኤፍሬም ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
9 ፤ ይኸውም በምናሴ ልጆች ርስት መካከል ለኤፍሬም ልጆች ከተለዩ ከተሞች ጋር፥ ከተሞች ሁሉ ከመንደሮቻቸው ጋር፥ ነው።
10 ፤ በጌዝርም የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላሳደዱአቸውም፥ እስከ ዛሬም ድረስ ከነዓናውያን በኤፍሬም መካከል ተቀምጠዋል፤ የጕልበት ግብርም ያስገብሩአቸው ነበር።