መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 21

የሌዋውያን አባቶች አለቆች ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ፥ ወደ እስራኤልም ልጆች ነገዶች አለቆች ቀረቡ፤
2 ፤ በከነዓን ምድር ባለችው በሴሎ። እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የምንቀመጥባቸውን ከተሞች፥ ለከብቶቻችንም መሰምርያዎች ትሰጡን ዘንድ አዝዞአል ብለው ተናገሩአቸው።
3 ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከርስታቸው እነዚህን ከተሞችና መሰምርያቸውን ለሌዋውያን ሰጡ።
4 ፤ ለቀዓትም ወገኖች ዕጣ ወጣ፤ ሌዋውያንም ለነበሩ ለካህኑ ለአሮን ልጆች ከይሁዳ ነገድ፥ ከስምዖንም ነገድ፥ ከብንያምም ነገድ አሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው።
5 ፤ ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ከኤፍሬም ነገድ፥ ከዳንም ነገድ፥ ከምናሴም ነገድ እኩሌታ አሥር ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው።
6 ፤ ለጌድሶንም ልጆች ከይሳኮር ነገድ፥ ከአሴርም ነገድ፥ ከንፍታሌምም ነገድ፥ በባሳንም ካለው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ አሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው።
7 ፤ ለሜራሪም ልጆች በየወገኖቻቸው ከሮቤል ነገድ፥ ከጋድም ነገድ፥ ከዛብሎንም ነገድ አሥራ ሁለት ከተሞች ሆኑላቸው።
8 ፤ እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች እነዚህን ከተሞችና መሰምርያቸውን ለሌዋውያን በዕጣ ሰጡ።
9 ፤ ከይሁዳም ልጆች ነገድ ከስምዖንም ልጆች ነገድ በስማቸው የተጠሩትን እነዚህን ከተሞች ሰጡ።
10 ፤ የፊተኛው ዕጣ ለእነርሱ ስለ ወጣ የሌዊ ልጆች የቀዓት ወገን ለሆኑ ለአሮን ልጆች ሆኑ።
11 ፤ በይሁዳ ተራራማ አገር ያለችውን ቂርያትአርባቅ የምትባለውን ከተማ በዙሪያዋም ያለውን መሰምርያ ሰጡአቸው፤ እርስዋም ኬብሮን ናት፥ ይህም አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ።
12 ፤ የከተማይቱን እርሻ ግን መንደሮችዋንም ለዮፎኔ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርገው ሰጡት።
13 ፤ ለካህኑም ለአሮን ልጆች እነዚህን ሰጡ፤ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ኬብሮንንና መሰምርያዋን፥ ልብናንና መሰምርያዋን፥
14 ፤ የቲርንና መሰምርያዋን፥ ኤሽትሞዓንና መሰምርያዋን፥
15 ፤ ሖሎንንና መሰምርያዋን፥ ዳቤርንና መሰምርያዋን፥
16 ፤ ዓይንንና መሰምርያዋን፥ ዮጣንና መሰምርያዋን፥ ቤትሳሚስንና መሰምርያዋን፤ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገዶች ዘጠኝ ከተሞችን ሰጡ።
17 ፤ ከብንያምም ነገድ ገባዖንንና መሰምርያዋን፥ ናሲብንና መሰምርያዋን፥
18 ፤ አናቶትንና መሰምርያዋን፥ አልሞንንና መሰምርያዋን፤ አራት ከተሞችን ሰጡ።
19 ፤ የአሮን ልጆች የካህናት ከተሞች ከመሰምርያቸው ጋር አሥራ ሦስት ናቸው።
20 ፤ ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ወገኖች ሌዋውያን የዕጣቸው ከተሞች ከኤፍሬም ነገድ ደረሱአቸው።
21 ፤ በኤፍሬም ተራራማ አገር ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ሴኬምንና መሰምርያዋን፥ ጌዝርንና መሰምርያዋን፥
22 ፤ ቂብጻይምንና መሰምርያዋን፥ ቤትሖሮንንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው።
23 ፤ ከዳንም ነገድ ኤልተቄንና መሰምርያዋን፥ ገባቶንንና መሰምርያዋን፥ ኤሎንንና መሰምርያዋን፥
24 ፤ ጋትሪሞንንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው።
25 ፤ ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ታዕናክንና መሰምርያዋን፥ ጋትሪሞንንና መሰምርያዋን፤ ሁለቱን ከተሞች ሰጡአቸው።
26 ፤ የቀሩት የቀዓት ልጆች ወገኖች ከተሞች ሁሉ ከመሰምርያቸው ጋር አሥር ናቸው።
27 ፤ ለሌዋውያንም ወገኖች ለጌድሶን ልጆች ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ በባሳን ውስጥ የሆነችውን ጎላንንና መሰምርያዋን፥ በኤሽትራንና መሰምርያዋን፤ ሁለቱን ከተሞች ሰጡአቸው።
28 ፤ ከይሳኮርም ነገድ ቂሶንንና መሰምርያዋን፥ ዳብራትንና መሰምርያዋን፥
29 ፤ የርሙትንና መሰምርያዋን፥ ዓይንጋኒምንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው።
30 ፤ ከአሴርም ነገድ ሚሽአልንና መሰምርያዋን፥ ዓብዶንንና መሰምርያዋን፥
31 ፤ ሔልቃትንና መሰምርያዋን፥ ረአብንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው።
32 ፤ ከንፍታሌምም ነገድ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን በገሊላ ውስጥ ቃዴስንና መሰምርያዋን፥ ሐሞትዶርንና መሰምርያዋን፥ ቀርታንንና መሰምርያዋን፤ ሦስቱን ከተሞች ሰጡአቸው።
33 ፤ የጌድሶን ልጆች ከተሞች ሁሉ በየወገኖቻቸው አሥራ ሦስት ከተሞች ከመሰምርያቸው ጋር ናቸው።
34 ፤ ከሌዋውያንም ለቀሩት ለሜራሪ ልጆች ወገን ከዛብሎን ነገድ ዮቅንዓምንና መሰምርያዋን፥
35 ፤ ቀርታንና መሰምርያዋን፥ ዲሞናንና መሰምርያዋን፥ ነህላልንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ።
36 ፤ ከሮቤልም ነገድ ቦሶርንና መሰምርያዋን፥ ያሀጽንና መሰምርያዋን፥
37 ፤ ቅዴሞትንና መሰምርያዋን፥ ሜፍዓትንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ።
38 ፤ ከጋድም ነገድ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን በገለዓድ ውስጥ ራሞትንና መሰምርያዋን፥ መሃናይምንና መሰምርያዋን፥
39 ፤ ሐሴቦንንና መሰምርያዋን፥ ኢያዜርንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ።
40 ፤ ከሌዋውያን ወገኖች የቀሩት የሜራሪ ልጆች ከተሞች ሁሉ በየወገኖቻቸው እነዚህ ነበሩ፤ ዕጣቸውም አሥራ ሁለት ከተማ ነበረ።
41 ፤ በእስራኤል ልጆች ርስት መካከል የነበሩት የሌዋውያን ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞችና መሰምርያቸው ነበሩ።
42 ፤ እነዚህም ከተሞች እያንዳንዳቸው ከመሰምርያቸው ጋር ነበሩ፤ እነዚህም ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ነበሩ።
43 ፤ እግዚአብሔርም ይሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ ወረሱአትም፥ ተቀመጡባትም።
44 ፤ እግዚአብሔርም ለአባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፤ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ ይቋቋማቸው ዘንድ ማንም ሰው አልቻለም፤ እግዚአብሔርም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው።
45 ፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም።