መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 17

ለምናሴ ነገድ ዕጣ ይህ ነው፤ የዮሴፍ በኵር እርሱ ነውና። የምናሴም በኵር የገለዓድ አባት ማኪር ብርቱ ሰልፈኛ ስለ ነበረ ገለዓድንና ባሳንን ወረሰ።
2 ፤ ዕጣውም ለቀሩት ለምናሴ ልጆች በየወገኖቻቸው፥ ለአቢዔዝር ልጆች፥ ለኬሌግ ልጆች፥ ለአሥሪኤል ልጆች፥ ለሴኬም ልጆች፥ ለኦፌር ልጆች፥ ለሸሚዳ ልጆች ሆነ፤ የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ወንዶች ልጆች በየወገኖቻቸው እነዚህ ናቸው።
3 ፤ ለምናሴ ልጅ፥ ለማኪር ልጅ፥ ለገለዓድ ልጅ፥ ለኦፌር ልጅ፥ ለሰለጰዓድ ግን ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም የሴቶች ልጆቹም ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ።
4 ፤ እነርሱም ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ ወደ አለቆችም ቀርበው። እግዚአብሔር በወንድሞቻችን መካከል ርስት እንዲሰጠን ሙሴን አዘዘ አሉ፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘ በአባታቸው ወንድሞች መካከል ርስት ሰጣቸው።
5 ፤ በዮርዳኖስ ማዶ ካለው ከገለዓድና ከባሳን አገር ሌላ ለምናሴ አሥር ዕጣ ሆነ፤
6 ፤ የምናሴ ሴቶች ልጆች በወንዶች ልጆች መካከል ርስት ተቀብለዋልና፤ የገለዓድም ምድር ለቀሩት ለምናሴ ልጆች ሆኖአልና።
7 ፤ የምናሴም ድንበር ከአሴር ጀምሮ በሴኬም ፊት ልፊት እስካለው እስከ ሚክምታት ድረስ ነበረ፤ ድንበሩም በቀኝ በኩል ወደ ዓይንታጱዋ ሰዎች አለፈ።
8 ፤ የታጱዋ ምድር ለምናሴ ነበረ፤ በምናሴ ዳርቻ ያለው ታጱዋ ግን ለኤፍሬም ልጆች ሆነ።
9 ፤ ድንበሩም ወደ ቃና ወንዝ ከወንዙ በደቡብ ወገን ወረደ፤ በምናሴም ከተሞች መካከል የነበሩት እነዚህ ከተሞች ለኤፍሬም ሆኑ፤ የምናሴም ድንበር በወንዙ በኩል በሰሜን ወገን ነበረ፥ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ።
10 ፤ በደቡብ በኩል ያለው ለኤፍሬም ነበረ፥ በሰሜንም በኩል ያለው ለምናሴ ነበረ፥ ድንበሩም ባሕሩ ነበረ፤ በሰሜን በኩል ወደ አሴር፥ በምሥራቅም በኩል ወደ ይሳኮር ደረሰ።
11 ፤ በይሳኮርና በአሴር መካከል ቤትሳንና መንደሮችዋ፥ ይብልዓምና መንደሮችዋ፥ ዶርና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ዓይንዶርና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ታዕናክና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ መጊዶና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ሦስቱ ኮረብቶች ለምናሴ ነበሩ።
12 ፤ የምናሴ ልጆች ግን የእነዚህን ከተሞች ሰዎች ሊያሳድዱአቸው አልቻሉም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ።
13 ፤ የእስራኤልም ልጆች በጸኑ ጊዜ ከነዓናውያንን የጕልበት ግብር አስገበሩአቸው፥ ፈጽመውም አላሳደዱአቸውም።
14 ፤ የዮሴፍ ልጆች ኢያሱን። እኔ ብዙ ሕዝብ ስለ ሆንሁ እስከ አሁንም እግዚአብሔር ስለ ባረከኝ ለምን አንድ ክፍል አንድም ዕጣ ብቻ ርስት አድርገህ ሰጠኸኝ? አሉት።
15 ፤ ኢያሱም። ብዙ ሕዝብስ ከሆንህ ተራራማውም የኤፍሬም አገር ጠብቦህ እንደ ሆነ ወደ ዱር ወጥተህ በፌርዛውያንና በራፋይም ምድር ለአንተ ስፍራ መንጥር አላቸው።
16 ፤ የዮሴፍም ልጆች። ተራራማው አገር አይበቃንም፤ በሸለቆውም ውስጥ ለሚኖሩት፥ በቤትሳንና በመንደሮችዋ በኢይዝራኤልም ሸለቆ ለሚኖሩት ከነዓናውያን የብረት ሰረገሎች አላቸው አሉት።
17 ፤ ኢያሱም የዮሴፍ ወገን ለሚሆኑ ለኤፍሬምና ለምናሴ። አንተ ብዙ ሕዝብ ነህ፥ ጽኑም ኃይል አለህ አንድ ዕጣ ብቻ አይሆንልህም፤
18 ፤ ነገር ግን ተራራማው አገር ለአንተ ይሆናል፥ ዱር እንኳን ቢሆንም ትመነጥረዋለህ፥ ለአንተም ይሆናል፤ ለከነዓናውያንም የብረት ሰረገሎች ቢሆኑላቸው የበረቱም ቢሆኑ ታሳድዳቸዋለህ አላቸው።