መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24


ምዕራፍ 23

እንዲህም ሆነ፤ ብዙ ዘመን ከሆነ በኋላ፥ እግዚአብሔርም እስራኤልን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፈ በኋላ፥ ኢያሱም በሸመገለ በዕድሜውም ባረጀ ጊዜ፥
2 ፤ ኢያሱ እስራኤልን ሁሉ ሽማግሌዎቻቸውንም አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምቶቻቸውንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው። እኔ ሸምግያለሁ፥ በዕድሜም አርጅቻለሁ፤
3 ፤ እናንተም አምላካቸሁ እግዚአብሔር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ስለ እናንተ ያደረገውን ሁሉ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋ እርሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነው።
4 ፤ እነሆ፥ እኔ ካጠፋኋቸው አሕዛብ ሁሉ ጋር ከዮርዳኖስ ጀምሮ በፀሐይ መግቢያ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ለነገዶቻችሁ ርስት እንዲሆኑ የቀሩትን እነዚህን አሕዛብ በዕጣ ከፈልሁላችሁ።
5 ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር እርሱ ከፊታችሁ በብርቱ ይበትናቸዋል፥ ከፊታችሁም ያሳድዳቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራችሁም ምድራቸውን ትወርሳላችሁ።
6 ፤ ስለዚህም በሙሴ ሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ በጣም በርቱ፥ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ።
7 ፤ በእናንተ መካከል ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ አትግቡ፤ የአማልክቶቻቸውንም ስም አትጥሩ፥ አትማሉባቸውም፥ አታምልኩአቸውም፥ አትስገዱላቸውም፤
8 ፤ እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጋችሁት ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተጠጉ እንጂ።
9 ፤ እግዚአብሔር ታላላቆችንና ኃይለኞችን አሕዛብ ከፊታችሁ አስወጥቶአል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም።
10 ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራችሁ ስለ እናንተ የሚዋጋ እርሱ ነውና ከእናንተ አንዱ ሰው ሺህ ሰውን ያሳድዳል።
11 ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱት ዘንድ ለራሳችሁ እጅግ ተጠንቀቁ።
12 ፤ እናንተ ግን ተመልሳችሁ በመካከላችሁ ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ ብትጠጉ፥ ከእነርሱም ጋር ብትጋቡ፥ እናንተም ወደ እነርሱ እነርሱም ወደ እናንተ ብትደራረሱ፥
13 ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስክትጠፉ ድረስ መውደቂያና ወጥመድ፥ በጎናችሁም መግረፊያ፥ በዓይናችሁም እሾህ ይሆኑባችኋል እንጂ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወዲያ እነዚህን አሕዛብ ከፊታችሁ እንዳያሳድዳቸው ፈጽማችሁ እወቁ።
14 ፤ እነሆም፥ ዛሬ የምድርን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፤ እናንተም እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል፤ ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም።
15 ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር የተናገረው መልካም ነገር ሁሉ እንደ ደረሰላችሁ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እናንተን እስኪያጠፋችሁ ድረስ እግዚአብሔር እንዲሁ ክፉን ነገር ሁሉ ያመጣባችኋል።
16 ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ስታፈርሱ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ስታመልኩ፥ ስትሰግዱላቸውም፥ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ይነድድባችኋል፥ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ።