መጽሐፈ ነህምያ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13


ምዕራፍ 3

ታላቁም ካህን ኤልያሴብ ወንድሞቹም ካህናት ተነሥተው የበግ በር ሠሩ፤ ቀደሱትም፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፤ እስከ ሃሜአ ግንብና እስከ ሐናንኤል ግንብ ድረስ ቀደሱት።
2 ፤ በአጠገቡ የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ በአጠገባቸውም የአምሪ ልጅ ዘኩር ሠራ።
3 ፤ የሃስናአ ልጆችም የዓሣ በር ሠሩ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ።
4 ፤ በአጠገባቸውም የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት አደሰ። በአጠገባቸውም የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም አደሰ። በአጠገባቸውም የበዓና ልጅ ሳዶቅ አደሰ።
5 ፤ በአጠገባቸውም ቴቁሐውያን አደሱ፤ ታላላቆቻቸው ግን ለጌታቸው ሥራ አንገታቸውን አላዋረዱም።
6 ፤ የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም አሮጌውን በር አደሱ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ።
7 ፤ በአጠገባቸውም ገባዖናዊው መልጥያና ሜሮኖታዊው ያዶን፥ የወንዙም ማዶ አለቃ ግዛት የሆኑ የገባዖንና የምጽጳ ሰዎች አደሱ።
8 ፤ በአጠገባቸውም ወርቅ አንጥረኛው የሐርሃያ ልጅ ዑዝኤል አደሰ። በአጠገቡም ከሽቱ ቀማሚዎች የነበረ ሐናንያ አደሰ፤ እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ ኢየሩሳሌምን ጠገኑ።
9 ፤ በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኵሌታ አለቃ የሆር ልጅ ረፋያ አደሰ።
10 ፤ በአጠገባቸውም የኤርማፍ ልጅ ይዳያ በቤቱ አንጻር ያለውን አደሰ። በአጠገቡም የአሰበንያ ልጅ ሐጡስ አደሰ።
11 ፤ የካሪም ልጅ መልክያ፥ የፈሐት ሞዓብ ልጅም አሱብ ሌላውን ክፍልና የእቶኑን ግንብ አደሱ።
12 ፤ በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኵሌታና የመንደሮችዋ አለቃ የአሎኤስ ልጅ ሰሎም አደሰ።
13 ፤ ሐኖንና የዛኖዋ ሰዎችም የሸለቆውን በር አደሱ፤ ሠሩት፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ፤ ደግሞም እስከ ጕድፍ መጣያው በር ድረስ አንድ ሺህ ክንድ የሚሆን ቅጥር ሠሩ።
14 ፤ የቤትሐካሪምም ግዛት አለቃ የሬካብ ልጅ መልክያ የጕድፍ መጣያውን በር አደሰ፤ ሠራው፥ ሳንቃዎቹንም አቆመ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ።
15 ፤ የምጽጳም ግዛት አለቃ የኮልሖዜ ልጅ ሰሎም የምንጩን በር አደሰ፤ ሠራው፥ ከደነውም፥ ሳንቃዎቹንም አቆመ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ፤ ከዳዊትም ከተማ እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ያለውን የሼላን መዋኛ ቅጥር ሠራ።
16 ፤ ከእርሱም በኋላ የቤትጹር ግዛት እኵሌታ አለቃ የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ በዳዊት መቃብር አንጻር እስካለው ስፍራ፥ እስከ ተሠራውም መዋኛ፥ እስከ ኃያላኑም ቤት ድረስ አደሰ።
17 ፤ ከእርሱም በኋላ ሌዋውያንና የባኒ ልጅ ሬሁም አደሱ። በአጠገባቸውም የቅዒላ ግዛት እኵሌታ አለቃ ሐሸብያ ስለ ግዛቱ አደሰ።
18 ፤ ከእርሱም በኋላ የቅዒላ ግዛት እኵሌታ አለቃ የኤንሐዳድ ልጅ በዋይ ወንድሞቹም አደሱ።
19 ፤ በአጠገቡም የምጽጳ አለቃ የኢያሱ ልጅ ኤጽር በማዕዘኑ አጠገብ በጦር መሣሪያ ቤት አንጻር ሌላውን ክፍል አደሰ።
20 ፤ ከእርሱም በኋላ የዘባይ ልጅ ባሮክ ከማዕዘኑ ጀምሮ እስከ ታላቁ ካህን እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ድረስ ሌላውን ክፍል ተግቶ አደሰ።
21 ፤ ከእርሱም በኋላ የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እስከ ኤልያሴብ ቤት መጨረሻ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ።
22 ፤ ከእርሱም በኋላ የቈላው ሰዎች ካህናቱ አደሱ።
23 ፤ ከእነርሱም በኋላ ብንያምና አሱብ በቤታቸው አንጻር ያለውን አደሱ። ከእነርሱም በኋላ የሐናንያ ልጅ የመዕሤያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን አደሰ።
24 ፤ ከእርሱም በኋላ የኤንሐደድ ልጅ ቢንዊ ከዓዛርያስ ቤት ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ።
25 ፤ የኡዛይ ልጅ ፋላል በማዕዘኑ አንጻር ያለውንና በዘበኞች አደባባይ አጠገብ ከላይኛው የንጉሡ ቤት ወጥቶ የቆመውን ግንብ ሠራ። ከእርሱም በኋላ የፋሮስ ልጅ ፈዳያ ሠራ።
26 ፤ ናታኒምም በዖፌል በውኃው በር አንጻር በምሥራቅ በኩል ወጥቶ በቆመው ግንብ አጠገብ እስካለው ስፍራ ድረስ ተቀመጡ።
27 ፤ ከእርሱም በኋላ ቴቁሐውያን ወጥቶ በቆመው በታላቁ ግንብ አንጻር ያለውን እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ሌላውን ክፍል አደሱ።
28 ፤ ከፈረሱ በር በላይ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየቤታቸው አንጻር አደሱ።
29 ፤ ከዚያ በኋላ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ አንጻር አደሰ። ከእርሱም በኋላ የምሥራቁን በር ጠባቂ የሴኬንያ ልጅ ሸማያ አደሰ።
30 ፤ ከእርሱ በኋላ የሰሌምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛው ልጁ ሐኖን ሌላውን ክፍል አደሱ። ከዚያም በኋላ የበራክያ ልጅ ሜሱላም በጓዳው አንጻር ያለውን አደሰ።
31 ፤ ከእርሱም በኋላ ከወርቅ አንጥረኞቹ የነበረ መልክያ እስከ ናታኒምና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት ድረስ በሐሚፍቃድ በር አንጻር ያለውን እስከ ማዕዘኑ መውጫ ድረስ አደሰ።
32 ፤ ከማዕዘኑም መውጫ ጀምረው እስከ በጉ በር ድረስ ወርቅ አንጥረኞችና ነጋዴዎች አደሱ።