መጽሐፈ መክብብ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 1

በኢየሩሳሌም የነገሠ የሰባኪው የዳዊት ልጅ ቃል።
2 ፤ ሰባኪው። ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል።
3 ፤ ከፀሐይ በታች በሚደክምበት ድካም ሁሉ የሰው ትርፉ ምንድር ነው?
4 ፤ ትውልድ ይሄዳል፥ ትውልድም ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ነው።
5 ፤ ፀሐይ ትወጣለች፥ ፀሐይም ትገባለች፥ ወደምትወጣበትም ስፍራ ትቸኵላለች።
6 ፤ ነፋስ ወደ ደቡብ ይሄዳል፥ ወደ ሰሜንም ይዞራል፤ ዘወትር በዙረቱ ይዞራል፥ ነፋስም በዙረቱ ደግሞ ይመለሳል።
7 ፤ ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፥ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደ ገና ወደዚያ ይመለሳሉ።
8 ፤ ነገር ሁሉ ያደክማል ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፤ ዓይን ከማየት አይጠግብም፥ ጆሮም ከመስማት አይሞላም።
9 ፤ የሆነው ነገር እርሱ የሚሆን ነው፥ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፤ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም።
10 ፤ ማንም። እነሆ፥ ይህ ነገር አዲስ ነው ይል ዘንድ ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተደርጎአል።
11 ፤ ለፊተኞቹ ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፤ ከኋለኞቹም ነገሮች ከእነርሱ በኋላ በሚነሡት ሰዎች ዘንድ መታሰቢያ አይገኝላቸውም።
12 ፤ እኔ ሰባኪው በእስራኤል ላይ በኢየሩሳሌም ንጉሥ ነበርሁ።
13 ፤ ከሰማይም በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ እፈልግና እመረምር ዘንድ ልቤን አተጋሁ፤ እግዚአብሔር ይደክሙባት ዘንድ ይህችን ለሰው ልጆች የሰጠ ክፉ ጥረት ናት።
14 ፤ ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
15 ፤ ጠማማ ይቀና ዘንድ አይችልም፤ ጐደሎም ይቈጠር ዘንድ አይችልም።
16 ፤ እኔ በልቤ። እነሆ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ላይ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ጥበብን አብዝቼ ጨመርሁ፤ ልቤም ብዙ ጥበብንና እውቀትን ተመለከተ ብዬ ተናገርሁ።
17 ፤ ጥበብንና ዕብደትን ሞኝነትንም አውቅ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፤ ይህም ደግሞ ነፋስን እንደ መከተል እንደ ሆነ አስተዋልሁ።
18 ፤ በጥበብ መብዛት ትካዜ ይበዛልና፤ እውቀትንም የሚጨምር ኀዘንን ይጨምራልና።