መጽሐፈ መክብብ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 2

እኔ በልቤ። ና በደስታም እፈትንሃለሁ፥ መልካምንም ቅመስ አልሁ፤ ይህም ደግሞ እነሆ ከንቱ ነበረ።
2 ፤ ሳቅን። ዕብድ ነህ፤ ደስታንም። ምን ታደርጋለህ? አልሁት።
3 ፤ የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች ሊሠሩት መልካም ነገር ምን እንደ ሆነ እስካይ ድረስ ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት ስንፍናንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ።
4 ፤ ትልቅ ሥራን ሠራሁ፥ ቤቶችንም አደረግሁ፥ ወይንም ተከልሁ፤
5 ፤ አትክልትንና ገነትን አደረግሁ፥ ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው፤
6 ፤ በዱር የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያ አደረግሁ።
7 ፤ ወንዶችንና ሴቶችን ባሪያዎች ገዛሁ፥ የቤት ውልድ ባሪያዎችም ነበሩኝ፤ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ ከብቶችና መንጋዎች ነበሩኝ።
8 ፤ ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ፤ አዝማሪዎችንና አርሆዎችን የሰዎች ልጆችንም ተድላ እጅግ የበዙ ሴቶችንም አከማቸሁ።
9 ፤ ታላቅም ሆንሁ፥ ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፤ ደግምም ጥበቤ ከእኔ ጋር ጸንታ ቀረች።
10 ፤ ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፤ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ።
11 ፤ እጄ የሠራቻችን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም።
12 ፤ እኔም ጥበብን ዕብደትንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ፤ በፊት ከተደረገው በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል?
13 ፤ እኔም ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ጥበብ ከስንፍና እንዲበልጥ አየሁ።
14 ፤ የጠቢብ ዓይኖች በራሱ ላይ ናቸው፥ ሰነፍ ግን በጨለማ ይሄዳል፤ ደግሞ ለሁለቱ መጨረሻቸው አንድ እንደ ሆነ አስተዋልሁ።
15 ፤ እኔም በልቤ። ለሰነፍ የሚደርሰው ለእኔም ይደርሳል፤ ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ? አልሁ። የዚያን ጊዜም በልቤ። ይህ ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ።
16 ፤ በሚመጣው ዘመን ነገር ሁሉ የተረሳ ይሆናልና ለዘላለም የሚሆን የጠቢብና የሰነፍ መታሰቢያ አይገኝም። አዬ ጉድ! ጠቢብ ከሰነፍ ጋር እንዴት ይሞታል!
17 ፤ ከፀሐይም በታች የተሠራው ሥራ ሁሉ ከብዶብኛልና ሕይወትን ጠላሁ፤ ሁሉም ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
18 ፤ ከእኔ በኋላ ለሚመጣው ሰው እተወዋለሁና ከፀሐይ በታች የደከምሁበትን ሁሉ ጠላሁት።
19 ፤ ጠቢብ ወይም ሰነፍ እንዲሆን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ከፀሐይ በታች በደከምሁበትና ጠቢብ በሆንሁበት በድካሜ ሁሉ ላይ ጌታ ይሆንበታል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።
20 ፤ እኔም ተመልሼ ልቤን ከፀሐይ በታች በደከምሁበት ድካም ሁሉ ተስፋ አስቈረጥሁት።
21 ፤ ሰው በጥበብና በእውቀት በብልሃትም ከደከመ በኋላ ለሌላ ላልደከመበት ሰው ያወርሰዋልና፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ትልቅም መከራ ነው።
22 ፤ ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ አሳብ የሰው ጥቅም ምንድር ነው?
23 ፤ ዘመኑ ሁሉ ኀዘን፥ ጥረትም ትካዜ ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።
24 ፤ ለሰው ከሚበላና ከሚጠጣ በድካሙም ደስ ከሚለው በቀር የሚሻለው ነገር የለም፤ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደ ተሰጠ አየሁ።
25 ፤ ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው?
26 ፤ እርሱም ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብንና እውቀትን ደስታንም ይሰጠዋል፤ ለኃጢአተኛ ግን እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ሰው ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ጥረትን ይሰጠዋል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።