መጽሐፈ መክብብ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 10

የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፤ እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል።
2 ፤ የጠቢብ ልብ በስተ ቀኙ ነው፥ የሰነፍ ልብ ግን በስተ ግራው ነው።
3 ፤ ደግሞም ሰነፍ በመንገድ ሲመላለስ እርሱ ልብ ይጐድለዋል፥ የሚያስበውም ሁሉ ስንፍና ነው።
4 ፤ ትዕግሥት ታላቁን ኃጢአት ጸጥ ያደርጋልና የገዢ ቍጣ የተነሣብህ እንደ ሆነ ስፍራህን አትልቀቅ።
5 ፤ ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም ከገዢ የሚወጣ ስሕተት ነው፤
6 ፤ ሰነፍ በታላቅ ማዕርግ ተሾመ፥ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ።
7 ፤ ባሪያዎች በፈረስ ላይ ሲቀመጡ መሳፍንትም እንደ ባሪያዎች በምድር ላይ ሲሄዱ አየሁ።
8 ፤ ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፥ ቅጥርንም የሚያፈርስን እባብ ትነድፈዋለች።
9 ፤ ድንጋይን የሚፈነቅል ይታመምበታል፥ እንጨትንም የሚፈልጥ ይጐዳበታል።
10 ፤ ብረት ቢደነዝዝ ሰውም ባይስለው ኃይልን ሊያበዛ ይገባዋል፤ ጥበብ ግን ሥራውን ለማከናወን ትጠቅመዋለች።
11 ፤ ደጋሚ ሳይደግምባት እባብ ብትነድፍ ለደጋሚው ትርፍ የለውም።
12 ፤ የጠቢብ ሰው የአፉ ቃል ሞገስ ናት፤ የሰነፍ ከንፈሮች ግን ራሱን ይውጡታል።
13 ፤ የአፉ ቃል መጀመሪያ ስንፍና ነው፥ የንግግሩ ፍጻሜም ክፉ እብደት ነው።
14 ፤ ሰነፍ ቃሉን ያበዛል፤ ሰው ግን የሚሆነውን አያውቅም፤ ከእርሱስ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል?
15 ፤ የሰነፍ ሥራ ያደክመዋል ወደ ከተማ መሄድ አያውቅምና።
16 ፤ ንጉሥሽ ሕፃን የሆነ፥ መኳንንቶችሽም ማልደው የሚበሉ፥ አንቺ አገር ሆይ፥ ወዮልሽ!
17 ፤ ንጉሥሽ የከበረ ልጅ የሆነ፥ ለብርታት እንጂ ለስካር ያይደለ በጊዜ የሚበሉ መኳንንት ያሉሽ፥ አንቺ አገር ሆይ፥ የተመሰገንሽ ነሽ።
18 ፤ ተግባር በመፍታት ጣራው ይዘብጣል፥ በእጅም መታከት ቤት ያፈስሳል።
19 ፤ እንጀራን ለሳቅ የወይን ጠጅንም ለሕይወት ደስታ ያደርጉታል፥ ሁሉም ለገንዘብ ይገዛል።
20 ፤ የሰማይ ወፍ ቃሉን ይወስደዋልና፥ ባለ ክንፎችም ነገሩን ይናገራሉና በልብህ አሳብ እንኳ ቢሆን ንጉሥን አትስደብ፥ በመኝታ ቤትህም ባለጠጋን አትስደብ።