መጽሐፈ መክብብ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 11

እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው፥ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኛዋለህና።
2 ፤ ለሰባት ደግሞም ለስምንት እድል ፈንታን ክፈል፥ በምድር ላይ የሚሆነውን ክፉ ነገር ምን እንደሆነ አታውቅምና።
3 ፤ ደመናት ዝናብ በሞሉ ጊዜ በምድር ላይ ያፈስሱታል፤ ዛፍም ወደ ደቡብ ወይም ወደ ሰሜን ቢወድቅ፥ ዛፉ በወደቀበት ስፍራ በዚያ ይኖራል።
4 ፤ ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፥ ደመናንም የሚመለከት አያጭድም።
5 ፤ የነፋስ መንገድ እንዴት እንደ ሆነች አጥንትም በእርጉዝ ሆድ እንዴት እንድትዋደድ እንደማታውቅ፥ እንዲሁም ሁሉን የሚሠራውን የእግዚአብሔርን ሥራ አታውቅም።
6 ፤ ወይም ይህ ወይም ያ ማናቸው እንዲበቅል ወይም ሁለቱ መልካም እንዲሆኑ አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ፥ በማታም እጅህን አትተው።
7 ፤ ብርሃን ጣፋጭ ነው ፀሐይንም ማየት ለዓይን መልካም ነው።
8 ፤ ሰው ብዙ ዘመን በሕይወት ቢኖር በሁሉም ደስ ይበለው፤ ሆኖም የጨለማውን ዘመን ያስብ፥ ብዙ ቀን ይሆናልና። የሚመጣው ነገር ሁሉ ከንቱ ነው።
9 ፤ አንተ ጐበዝ፥ በጕብዝናህ ደስ ይበልህ፥ በጕብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፥ በልብህም መንገድ ዓይኖችህም በሚያዩት ሂድ፤ ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ እወቅ።
10 ፤ ሕፃንነትና ጕብዝና ከንቱዎች ናቸውና ከልብህ ኀዘንን አርቅ፥ ከሰውነትህም ክፉን ነገር አስወግድ።