ትንቢተ ሆሴዕ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 12

ኤፍሬም በሐሰት፥ የእስራኤልም ቤት በተንኰል ከበበኝ፤ ይሁዳም ከታመነው ቅዱሱ ከእግዚአብሔር ጋር አይጸናም።
2 ፤ ኤፍሬም ነፋስን ይበላል፥ የምሥራቅንም ነፋስ ይከተላል፤ ሁልጊዜም ሐሰትንና ተንኰልን ያበዛል፤ ከአሦር ጋር ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፥ ወደ ግብጽም ዘይት ይወስዳሉ።
3 ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ ከይሁዳ ጋር ክርክር አለው፥ ያዕቆብንም እንደ መንገዱ ይቀጣል፤ እንደ ሥራውም ይመልስለታል።
4 ፤ በማኅፀን ውስጥ ወንድሙን በተረከዙ ያዘው፥ በጕልማስነቱም ጊዜ ከአምላክ ጋር ታገለ፤
5 ፤ ከመልአኩም ጋር ታግሎ አሸነፈ፤ አልቅሶም ለመነው። በቤቴልም አገኘው፥ በዚያም ከእኛ ጋር ተነጋገረ።
6 ፤ እርሱም የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ የመታሰቢያው ስም እግዚአብሔር ነው።
7 ፤ ስለዚህ ወደ አምላክህ ተመለስ፤ ምሕረትንና ፍርድን ጠብቅ፥ ዘወትርም በአምላክህ ታመን።
8 ፤ ከከነዓን ወገን ነው፤ በእጁ የተንኰል ሚዛን አለ፥ ሽንገላንም ይወድዳል።
9 ፤ ኤፍሬምም። ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ፥ ሀብትንም አግኝቻለሁ፥ በድካሜም ሁሉ ኃጢአት የሚሆን በደል አይገኝብኝም አለ።
10 ፤ እኔም ከግብጽ ጀምሬ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንደ ዓመት በዓል ቀን እንደ ገና በድንኳን እንድትኖር አደርግሃለሁ።
11 ፤ ለነቢያትም ተናግሬአለሁ፥ ራእይንም አብዝቻለሁ፤ በነቢያትም እጅ ምሳሌዎችን አውጥቻለሁ።
12 ፤ ኃጢአት በገለዓድ አለ፤ ፈጽመው ከንቱ ናቸው፤ ወይፈኖች በጌልገላ ይሠዋሉ፥ መሠዊያዎቻቸውም በእርሻ ትልም ላይ የድንጋይ ክምር ይሆናሉ።
13 ፤ ያዕቆብ ወደ ሶርያ አገር ሸሸ፥ እስራኤልም ስለ ሚስት አገለገለ፥ ስለ ሚስትም ጠባቂ ነበረ።
14 ፤ እግዚአብሔርም በነቢይ እጅ እስራኤልን ከግብጽ አወጣ፥ በነቢይም እጅ ጠበቀው።
[15]፤ ኤፍሬም አስመርሮ አስቈጣው፤ ስለዚህ ደሙ በላዩ ላይ ነው፤ ጌታውም ስድቡን በራሱ ላይ ይመልሳል።