ትንቢተ ሆሴዕ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 2

የእስራኤልም ልጆች ቍጥር እንደማይሰፈርና እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም ተብሎ በተነገረበት በዚያ ስፍራ የሕያው አምላክ ልጆች ይባላሉ።
2 ፤ የይሁዳ ልጆችና የእስራኤል ልጆች በአንድነት ይሰበሰባሉ፥ ለእነርሱም አንድ አለቃ ይሾማሉ፥ ከምድሪቱም ይወጣሉ፤ የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሆናልና።
3 ፤ ወንድሞቻችሁን። ዓሚ፥ እኅቶቻችሁንም። ሩሃማ በሉአቸው።
4 ፤ እናታችሁ ሚስቴ አይደለችምና፥ እኔም ባልዋ አይደለሁምና ተምዋገቱ፤ ከእናታችሁ ጋር ተምዋገቱ። ግልሙትናዋን ከፊትዋ፥ ምንዝርናዋንም ከጡቶችዋ መካከል ታስወግድ፤
5 ፤ ዕራቁትዋን እንዳልገፍፋት፥ እንደ ተወለደችበትም ቀን እንዳላደርጋት፥ እንደ ምድረ በዳና እንደ ደረቅ ምድር እንዳላደርጋት፥ በጥማትም እንዳልገድላት፤
6 ፤ የግልሙትናዋ ልጆች ናቸውና ልጆችዋን አልምርም።
7 ፤ እናታቸው አመንዝራለች፤ የፀነሰቻቸውም። እንጀራዬንና ውኃዬን፥ ጥጤንና የተልባ እግሬን፥ ዘይቴንና መጠጤን ከሚሰጡኝ ከውሽሞቼ በኋላ እሄዳለሁ ብላ አስነወረቻቸው።
8 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ መንገድሽን በእሾህ እዘጋለሁ፥ መንገድዋንም እንዳታገኝ ቅጥርን እቀጥርባታለሁ።
9 ፤ ውሽሞችዋንም ትከተላለች፥ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸውማለች፥ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ እርስዋም። ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ ትላለች።
10 ፤ እርስዋም እህልንና ወይንን ጠጅ ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም የተሠራውን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም።
11 ፤ ስለዚህ እህሌን በጊዜዋ፥ ወይን ጠጄንም በወረትዋ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም እንዳትሸፍን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ።
12 ፤ አሁንም ውሽሞችዋ እያዩ ነውርዋን እገልጣለሁ፤ ከእጄም ማንም አያድናትም።
13 ፤ ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ የተቀደሱትንም ጉባኤዎችን ሁሉ አስቀራለሁ።
14 ፤ እርስዋም። ውሽሞቼ የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው ያለችውን ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፤ ዱርም አደርገዋለሁ፥ የምድረ በዳም አራዊት ይበሉታል።
15 ፤ እኔን ረስታ ውሽሞችዋን እየተከተለች፥ በጕትቾችዋና በጌጥዋም እያጌጠች ለበኣሊም ያጠነችበትን ወራት እበቀልባታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
16 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ።
17 ፤ ከዚያም የወይን ቦታዋን፥ የተስፋ በርም እንዲሆንላት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤ በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ሕፃንነትዋ ወራት ትዘምራለች።
18 ፤ በዚያ ቀን ባሌ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ በኣሌ ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል እግዚአብሔር፤
19 ፤ የበኣሊምን ስም ከአፍዋ አስወግደዋለሁና፥ በስማቸውም እንግዲህ አይታሰቡምና።
20 ፤ በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ከመሬትም ተንቀሳቃሾች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ቀስትንና ሰይፍን ሰልፍንም ከምድሩ እሰብራለሁ፥ ተከልለውም እንዲኖሩ አስተኛቸዋለሁ።
21 ፤ ለዘላለምም ለእኔ እንድትሆኚ አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ በምሕረትና በርኅራኄ አጭሻለሁ።
22 ፤ ለእኔም እንድትሆኚ በመታመን አጭሻለሁ፤ አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂአለሽ።
23 ፤ በዚያንም ቀን እመልሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለሰማይ እመልሳለሁ፥ ሰማይም ለምድር ይመልሳል፤
[24]፤ ምድርም ለእህልና ለወይን ጠጅ ለዘይትም ትመልሳለች፤ እነርሱም ለኢይዝራኤል ይመልሳሉ።
[25]፤ በምድርም ላይ ለእኔ እዘራታለሁ፤ ምሕረትም የሌላትን እምራለሁ፥ ሕዝቤም ያልሆነውን። አንተ ሕዝቤ ነህ እለዋለሁ፤ እርሱም። አንተ አምላኬ ነህ ይለኛል።