ትንቢተ ሆሴዕ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 6

ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል።
2 ፤ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፥ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን።
3 ፤ እንወቅ፤ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፤ እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፤ እንደ ዝናብም ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ መጨረሻ ዝናብ ይመጣል።
4 ፤ ምሕረታችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ፥ ምን ላድርግልህ?
5 ፤ ስለዚህ በነቢያት እጅ ቈረጥኋቸው፥ በአፌም ቃል ገደልኋቸው፤ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል።
6 ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና።
7 ፤ እነርሱ ግን እንደ አዳም ቃል ኪዳንን ተላልፈዋል፤ በዚያም ላይ ወንጅለውኛል።
8 ፤ ገለዓድ ኃጢአትን የሚሠሩ ሰዎች ከተማ፥ በደምም የተቀባ ነው።
9 ፤ ለሰውም እንደሚያደቡ ወንበዴዎች፥ እንዲሁ የካህናት ወገኖች በሴኬም መንገድ ላይ ይገድላሉ፤ ሴሰኝነትንም ያደርጋሉ።
10 ፤ በእስራኤል ቤት የሚያስፈራን ነገር አይቻለሁ፤ በዚያ በኤፍሬም ውስጥ ግልሙትና ተገኘ፥ እስራኤልም ረክሶአል።
11 ፤ ይሁዳ ሆይ፥ የሕዝቤን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ ለአንተ ደግሞ መከር ተወስኖልሃል።