ትንቢተ ሆሴዕ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 7

በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በውጭም ወንበዴዎች ቀምተዋልና እስራኤልን እፈውስ ዘንድ በወደድሁ ጊዜ የኤፍሬም ኃጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ።
2 ፤ እኔም ክፋታቸውን ሁሉ እንዳሰብሁ በልባቸው አያስቡም አሁንም ሥራቸው ከብባቸዋለች፥ በፊቴም አለች።
3 ፤ ንጉሡን በክፋታቸው፥ አለቆቹንም በሐሰታቸው ደስ አሰኝተዋል።
4 ፤ ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፤ ጋጋሪ እንደሚያነድድበት እንደ ምድጃ ናቸው፤ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ እሳትን መቈስቈስና እርሾን መለወስ ይቆያል።
5 ፤ በንጉሣችን ቀን አለቆች ከወይን ጠጅ ሙቀት የተነሣ ታመሙ፤ እርሱም ከዋዘኞች ጋር እጁን ዘረጋ።
6 ፤ እያደቡ ልባቸውን እንደ ምድጃ አዘጋጅተዋል፤ አበዛቸውም ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፤ በጠባም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ይነድዳል።
7 ፤ ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፥ ፈራጆቻቸውንም በሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወደቁ፤ ከእነርሱም ወደ እኔ የሚጮኽ የለም።
8 ፤ ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፤ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ነው።
9 ፤ እንግዶች ጕልበቱን በሉት፥ እርሱም አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም።
10 ፤ የእስራኤልም ትዕቢቱ በፊቱ መሰከረ፤ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም።
11 ፤ ኤፍሬምም አእምሮ እንደሌላት እንደ ሰነፍ ርግብ ነው፤ ግብጽን ጠሩ፥ ወደ አሦርም ሄዱ።
12 ፤ ሲሄዱ አሽክላዬን አዘረጋባቸዋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎች አወርዳቸዋለሁ፤ መከራቸውን ሲሰሙ እገሥጻቸዋለሁ።
13 ፤ ከእኔ ፈቀቅ ብለዋልና ወዮላቸው! በእኔም ላይ ዐመፀዋልና ጥፋት ይምጣባቸው! እኔ ልታደጋቸው ወደድሁ፥ እነርሱ ግን በሐሰት ተናገሩብኝ።
14 ፤ በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፤ በእኔም ላይ ዐመፁ።
15 ፤ እኔም ክንዳቸውን አስተማርሁና አጸናሁ፤ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን መከሩብኝ።
16 ፤ ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፤ እንደ ተንኰለኛ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸው ከምላሳቸው ቍጣ የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህ በግብጽ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።