ትንቢተ ዘካርያስ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 11

ሊባኖስ ሆይ፥ ደጆችህን ክፈት፥ እሳትም ዝግባዎችህን ትብላ።
2 ፤ የጥድ ዛፍ ሆይ፥ ዝግባ ወድቆአልና፥ ከበርቴዎችም ጠፍተዋልና ዋይ በል፤ እናንተም የባሳን ዛፎች ሆይ፥ ጽኑው ጫካ ተቈርጦአልና ዋይ በሉ።
3 ፤ የእረኞች ክብር ተዋርዶአልና የዋይታቸው ድምፅ ተሰምቶአል፤ የዮርዳኖስ ትዕቢት ተዋርዶአልና የአንበሶች ግሣት ድምፅ ተሰምቶአል።
4 ፤ አምላኬ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል። ለእርድ የሚሆኑትን በጎች ጠብቅ።
5 ፤ የገዙአቸው ያርዱአቸዋል፥ ራሳቸውንም እንደ በደለኞች አድርገው አይቈጥሩም፤ የሸጡአቸውም። ባለ ጠጋ ሆነናልና እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ፤ እረኞቻቸውም አይራሩላቸውም።
6 ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ ለሚኖሩ አልራራም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነሆም፥ ሰውን ሁሉ በባልንጀራውና በንጉሡ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ምድሪቱንም ይመታሉ፥ ከእጃቸውም አላድናቸውም።
7 ፤ እኔም ለእርድ የሚሆኑትን በጎች፥ የመንጋውን ችግረኞች ጠበቅሁ። ሁለት በትሮችንም ወሰድሁ፤ የአንዲቱን ስም ውበት የሁለተኛይቱንም ስም ማሰሪያ ብዬ ጠራሁ፤ መንጋውንም ጠበቅሁ።
8 ፤ በአንድ ወርም ሦስቱን እረኞች አጠፋሁ፤ ነፍሴም ተሰቀቀቻቸው፥ ነፍሳቸውም ደግሞ እኔን ጠላች።
9 ፤ እኔም። እናንተን አልጠብቅም፤ የሚሞተው ይሙት፥ የሚጠፋውም ይጥፋ፤ የቀረውም እያንዳንዱ የባልንጀራውን ሥጋ ይብላ አልሁ።
10 ፤ እኔም ከሕዝቦች ሁሉ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አፈርስ ዘንድ ውበት የተባለችውን በትሬን ወስጄ ቈረጥሁ።
11 ፤ በዚያም ቀን ተሰበረች፤ እንዲሁም እኔን የተመለከቱ የመንጋው ችግረኞች የእግዚአብሔር ቃል እንደ ነበረ አወቁ።
12 ፤ እኔም። ደስ ብሎአችሁ እንደ ሆነ ዋጋዬን ስጡኝ፤ ያለዚያ ግን ተዉት አልሁ። እነርሱም ለዋጋዬ ሠላሳ ብር መዘኑ።
13 ፤ እግዚአብሔርም። የተስማሙበትን የከበረውን ዋጋዬን በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው አለኝ። እኔም ሠላሳውን ብር ወስጄ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኖርሁት።
14 ፤ በይሁዳና በእስራኤል መካከል ያለውንም ወንድማማችነት እሰብር ዘንድ ማሰሪያ የተባለችውን ሁለተኛይቱን በትሬን ቈረጥሁ።
15 ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ዳግመኛም የሰነፍን እረኛ ዕቃ ውሰድ።
16 ፤ እነሆ፥ በአገሩ ውስጥ እረኛ አስነሣለሁ፤ እርሱም የጠፋውን አያስብም፥ የባዘነውን አይፈልግም፥ የተሰበረውን አይጠግንም፤ የዳነውንም አይቀልብም፥ ነገር ግን የሰባውን ሥጋ ይበላል፥ ሰኰናውንም ይቀለጣጥማል።
17 ፤ መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት! ሰይፍ በክንዱና በቀኝ ዓይኑ ላይ ይሆናል፤ ክንዱም አጥብቃ ትደርቃለች፥ ቀኝ ዓይኑም ፈጽሞ ትጨልማለች።