ትንቢተ ዘካርያስ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 12

ስለ እስራኤል የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም ይህ ነው። ሰማያትን የዘረጋ፥ ምድርንም የመሠረተ፥ የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
2 ፤ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ላሉት ለአሕዛብ ሁሉ የመንገድገድ ዋንጫ አደርጋታለሁ፤ ደግሞም ኢየሩሳሌም ስትከበብ በይሁዳ ላይ እንዲሁ ይሆናል።
3 ፤ በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፤ የሚሸከሙአት ሁሉ እጅግ ይቈስላሉ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በላይዋ ላይ ይከማቻሉ።
4 ፤ በዚያ ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ፈረስን ሁሉ በድንጋጤ፥ ተቀማጭንም በእብድነት እመታለሁ፤ ዓይኖቼንም በይሁዳ ላይ እከፍታለሁ፥ የአሕዛብንም ፈረሶች ሁሉ በዕውርነት እመታለሁ።
5 ፤ የይሁዳም አለቆች በልባቸው። በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ በአምላካቸው በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ብርታት አለ ይላሉ።
6 ፤ በዚያ ቀን የይሁዳን አለቆች በእንጨት መካከል እንዳለ ትንታግ፥ በነዶችም መካከል እንዳለ እንደ ፋና ነበልባል አደርጋቸዋለሁ፤ በቀኝና በግራ በዙሪያ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይበላሉ፤ ከዚያም ወዲያ ኢየሩሳሌም በስፍራዋ በኢየሩሳሌም ትኖራለች።
7 ፤ እግዚአብሔርም የዳዊት ቤት ክብርና የኢየሩሳሌም ሰዎች ክብር በይሁዳ ክብር ላይ እንዳይታበይ የይሁዳን ድንኳኖች አስቀድሞ ያድናል።
8 ፤ በዚያ ቀን እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ይመክትላቸዋል፤ በዚያም ቀን ከእነርሱ መካከል ደካማው እንደ ዳዊት ይሆናል፤ የዳዊትም ቤት በፊታቸው እንደ እግዚአብሔር መልአክ እንደ አምላክ ይሆናል።
9 ፤ በዚያም ቀን በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጡትን አሕዛብ ሁሉ ለማጥፋት እጋደላለሁ።
10 ፤ በዳዊትም ቤት ላይ፥ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ላይ፥ የሞገስንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ፤ ወደ እርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ፤ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል።
11 ፤ በዚያ ቀን በመጊዶን ሜዳ እንደ ነበረው እንደ ሐዳድሪሞን ልቅሶ ታላቅ ልቅሶ በኢየሩሳሌም ይሆናል።
12 ፤ ምድሪቱም ታለቅሳለች፤ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ የዳዊት ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ የናታን ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤
13 ፤ የሌዊ ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ የሰሜኢ ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤
14 ፤ የቀሩት ወገኖች ሁሉ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው ያለቅሳሉ።