ትንቢተ ዘካርያስ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 9

የእግዚአብሔር ቃል ሸክም በሴድራክ ምድር ላይ ነው፥ በደማስቆም ላይ ያርፋል፤ የእግዚአብሔር ዓይን ወደ ሰውና ወደ እስራኤል ነገድ ሁሉ ዘንድ ነው፤
2 ፤ ደግሞም በዳርቻዋ ባለችው በሐማት ላይ፥ እጅግ ጠቢበኞች በሆኑ በጢሮስና በሲዶና ላይ ነው።
3 ፤ ጢሮስም ምሽግን ለራስዋ ሠርታለች፥ ብሩንም እንደ አፈር ጥሩውንም ወርቅ እንደ መንገድ ጭቃ አከማችታለች።
4 ፤ እነሆ፥ ጌታ ይገፍፋታል፥ በባሕርም ላይ ያለውን ብርታትዋን ይመታል፤ እርስዋም በእሳት ትበላለች።
5 ፤ አስቀሎና አይታ ትፈራለች፤ ጋዛ ደግሞ አይታ እጅግ ትታመማለች፤ አቃሮንም እንዲሁ፥ ተስፋዋ ይቈረጣልና፤ ንጉሡም ከጋዛ ይጠፋል፥ በአስቀሎናም የሚቀመጥ አይገኝም።
6 ፤ የተደባለቀ ወገን በአዛጦን ይቀመጣል፥ የፍልስጥኤማውያንንም ትዕቢት አጠፋለሁ።
7 ፤ ደሙንም ከአፉ ውስጥ ርኩሱንም ነገር ከጥርሱ መካከል አስወግዳለሁ፤ እርሱም ደግሞ ለአምላካችን ቅሬታ ይሆናል፤ በይሁዳም እንደ አለቃ ይሆናል፥ አቃሮንም እንደ ኢያቡሳዊ ይሆናል።
8 ፤ እኔም ማንም እንዳይሄድና እንዳይመለስ እንደ ጠባቂ ጦር ሆኖ በቤቴ ዙሪያ ሰፈር አደርጋለሁ፤ አሁንም በዓይኔ አይቻለሁና ከዚህ በኋላ አስጨናቂ አያልፍባቸውም።
9 ፤ አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።
10 ፤ ሰረገላውንም ከኤፍሬም ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም አጠፋለሁ፤ የሰልፉም ቀስት ይሰበራል፥ ለአሕዛብም ሰላምን ይናገራል፤ ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፥ ከወንዙም እስከ ምድር ዳርቻ ድርስ ይሆናል።
11 ፤ ለአንቺም ደግሞ ስለ ቃል ኪዳንሽ ደም፥ እስሮችሽን ውኃ ከሌለበት ጕድጓድ አውጥቻለሁ።
12 ፤ እናንተ በተስፋ የምትኖሩ እስሮች ሆይ፥ ወደ ጽኑ አምባ ተመለሱ፤ ሁለት እጥፍ አድርጌ እንድመልስልሽ ዛሬ እነግርሻለሁ።
13 ፤ ይሁዳን ለእኔ ገትሬአለሁ፤ ቀስቱን በኤፍሬም ሞልቼአለሁ፤ ጽዮን ሆይ፥ ልጆችሽን በግሪክ ልጆች ላይ አስነሣለሁ፥ አንቺንም እንደ ኃያል ሰው ሰይፍ አደርግሻለሁ።
14 ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ይገለጣል፥ ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይወጣል፤ ጌታ እግዚአብሔርም መለከትን ይነፋል፥ በደቡብም ዐውሎ ነፋስ ይሄዳል።
15 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይጠብቃቸዋል፤ እነርሱም ይበሉአቸዋል፥ የወንጭፉንም ድንጋዮች ይረግጣሉ፤ እንደ ወይን ጠጅም ይጠጡአቸዋል፥ እንደ ጥዋዎችም እንደ መሠዊያም ማዕዘኖች የተሞሉ ይሆናሉ።
16 ፤ በዚያም ቀን አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ሕዝቡ መንጋ ያድናቸዋል፤ እነርሱም ለአክሊል እንደሚሆኑ እንደ ከበሩ ድንጋዮች ይሆናሉ፥ በምድሩም ላይ ይብለጨለጫሉ።
17 ፤ በጎነቱ እንዴት ታላቅ ነው! ውበቱስ እንዴት ታላቅ ነው! እህል ጐበዛዝቱን፥ ጉሽ ጠጅም ቈነጃጅቱን ያለመልማል።