ትንቢተ ዘካርያስ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 6

ተመልሼም ዓይኖቼን አነሣሁ፥ እነሆም፥ አራት ሰረገሎች ከሁለት ተራራ መካከል ሲወጡ አየሁ፤ ተራሮቹም የናስ ተራሮች ነበሩ።
2 ፤ በፊተኛው ሰረገላ መጋላ ፈረሶች፥ በሁለተኛውም ሰረገላ ዱሪ ፈረሶች ነበሩ፥
3 ፤ በሦስተኛውም ሰረገላ አምባላይ ፈረሶች፥ በአራተኛውም ሰረገላ ቅጥልጣል ፈረሶች ነበሩ።
4 ፤ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ። ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት።
5 ፤ መልአኩም መልሶ። እነዚህ በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ከቆሙበት ስፍራ የሚወጡ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ናቸው።
6 ፤ ዱሪ ፈረሶች ያሉበት ወደ ሰሜን ይወጣል፤ አምባላዮቹም ከእነርሱ በኋላ ይወጣሉ፥ ቅጥልጣሎችም ወደ ደቡብ ይወጣሉ አለኝ።
7 ፤ መጋላዎቹም ደግሞ ወጡ በምድርም ይመላለሱ ዘንድ ለመሄድ ይፈልጉ ነበር፤ እርሱም። ሂዱ፥ በምድር ላይ ተመላለሱ አለ። እነርሱም በምድር ላይ ተመላለሱ።
8 ፤ ጮኾም። እነሆ፥ ወደ ሰሜን ምድር የሚወጡት እነርሱ መንፈሴን በሰሜን ምድር ላይ አሳርፈዋል ብሎ ተናገረኝ።
9 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
10 ፤ ከባቢሎን ከመጡት ምርኮኞች ከሔልዳይና ከጦብያ ከዮዳኤም ውሰድ፤ በዚያም ቀን መጥተህ ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ግባ።
11 ፤ ብርንና ወርቅን ከእነርሱ ውሰድ፥ አክሊሎችንም ሥራ፤ በታላቁም ካህን በኢዮሴዴቅ ልጅ በኢያሱ ራስ ላይ ድፋቸው፥
12 ፤ እንዲህም በለው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ስሙ ቍጥቋጥ የሚባል ሰው በስፍራው ይበቅላል፥ የእግዚአብሔርንም መቅደስ ይሠራል።
13 ፤ እርሱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠራል፥ ክብርንም ይሸከማል፥ በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይነግሣል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፥ የሰላምም ምክር በሁለቱ መካከል ይሆናል።
14 ፤ አክሊሎችም ለሔሌምና ለጦብያ ለዮዳኤም ለሶፎንያስም ልጅ ለሔን በእግዚአብሔር መቅደስ ውስጥ ለመታሰቢያ ይሆናሉ።
15 ፤ በሩቅም ያሉት መጥተው የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠራሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቃችሁ ብትሰሙ ይህ ይሆናል።