መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን

1 2 3 4 5 6 7 8


ምዕራፍ 2

እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ።
2 ፤ በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ናት።
3 ፤ በዱር እንዳለ እንኮይ፥ እንዲሁ ውዴ በልጆች መካከል ነው። ከጥላው በታች እጅግ ወድጄ ተቀመጥሁ፥ ፍሬውም በጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው።
4 ፤ ወደ ወይን ጠጁም ቤት አገባኝ፥ በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው።
5 ፤ በዘቢብም አጽናኑኝ፥ በእንኮይ አበረታቱኝ፥ በፍቅሩ ተነድፌ ታምሜያለሁና።
6 ፤ ግራው ከራሴ በታች ናት፥ ቀኙም ታቅፈኛለች።
7 ፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሱትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አምላችኋለሁ።
8 ፤ እነሆ፥ የውዴ ቃል! በተራሮች ላይ ሲዘልል፥ በኮረብቶችም ላይ ሲወረወር ይመጣል።
9 ፤ ውዴ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ይመስላል፤ እነሆ፥ በመስኮቶች ሲጐበኝ፥ በዓይነ ርግብም ሲመለከት፥ እርሱ ከቅጥራችን በኋላ ቆሞአል።
10 ፤ ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ። ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ።
11 ፤ እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ።
12 ፤ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ።
13 ፤ በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ።
14 ፤ በዓለት ንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ፥ ቃልሽ መልካም ፊትሽም ያማረ ነውና መልክሽን አሳዪኝ፥ ድምፅሽንም አሰሚኝ።
15 ፤ ወይናችን አብቦአልና የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ቀበሮች፥ ጥቃቅኑን ቀበሮች አጥምዳችሁ ያዙልን።
16 ፤ ውዴ የእኔ ነው፥ እኔም የእርሱ ነኝ፤ በሱፍ አበባዎች መካከልም መንጋውን ያሰማራል።
17 ፤ ውዴ ሆይ፥ ቀኑ እስኪነፍስ፥ ጥላውም እስኪሸሽ ድረስ ተመለስ፤ በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋውን ወይም የዋላውን እምቦሳ ምሰል።