መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን

1 2 3 4 5 6 7 8


ምዕራፍ 3

ሌሊት በምንጣፌ ላይ ነፍሴ የወደደችውን ፈለግሁት፤ ፈለግሁት አላገኘሁትም።
2 ፤ እነሣለሁ በከተማይቱም እዞራለሁ፥ ነፍሴ የወደደችውን በጎዳናና በአደባባይ እፈልጋለሁ፤ ፈለግሁት አላገኘሁትም።
3 ፤ ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ ነፍሴ የወደደችውን አያችሁትን? አልኋቸውም።
4 ፤ ከእነርሱም ጥቂት እልፍ ብዬ ነፍሴ የወደደችውን አገኘሁት፥ ያዝሁትም ወደ እናቴም ቤት ወደ ወላጅ እናቴም እልፍኝ እስካገባው ድረስ አልተውሁትም።
5 ፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሡትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አምላችኋለሁ።
6 ፤ መዓዛም እንደ ከርቤና እንደ ዕጣን የሆነችው፥ ከልዩ ከነጋዴ ቅመም ሁሉ የሆነችው፥ ይህች ከምድረ በዳ እንደ ጢስ ምስሶ የወጣችው ማን ናት?
7 ፤ እነሆ፥ የሰሎሞን አልጋ ናት፤ ከእስራኤል ኃያላን ስድሳ ኃያላን በዙሪያው ናቸው።
8 ፤ ሁሉም ሰይፍ የያዙ ሰልፈኞች ናቸው፤ በሌሊት ከሚወድቀው ፍርሃት የተነሣ ሰው ሁሉ ሰይፉ በወገቡ አለ።
9 ፤ ንጉሡ ሰሎሞን መሸከሚያን ከሊባኖስ እንጨት ለራሱ አሠራ።
10 ፤ ምሰሶቹን የብር፥ መደገፊያውንም የወርቅ፥ መቀመጫውንም ሐምራዊ ግምጃ አደረገ፤ ውስጡ በኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ፍቅር የተለበጠ ነው።
11 ፤ እናንተ የጽዮን ቈነጃጅት፥ ውጡ፤ እናቱ በሠርጉ ቀንና በልቡ ደስታ ቀን ያደረገችለትን አክሊል ደፍቶ ንጉሥ ሰሎሞንን እዩ።