መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን

1 2 3 4 5 6 7 8


ምዕራፍ 8

አንተ የእናቴን ጡት እንደ ጠባ እንደ ወንድሜ ምነው በሆንህ! በሜዳ ባገኘሁህ ጊዜ በሳምሁህ፥ ማንም ባልናቀኝም ነበር።
2 ፤ መርቼ ወደ እናቴ ቤት ባገባሁህ፥ በዚያም አንተ ባስተማርከኝ፤ እኔም ከመልካሙ ወይን ጠጅ ከሮማኔም ውኃ ባጠጣሁህ ነበር።
3 ፤ ግራው ከራሴ በታች በሆነች ቀኙም ባቀፈችኝ ነበር።
4 ፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ ፍቅርን እንዳታስነሡት እንዳታነሣሡትም አምላችኋለሁ።
5 ፤ በውድዋ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት? ከእንኮይ በታች አስነሣሁህ፤ በዚያ እናትህ ወለደችህ፥ በዚያም ወላጅ እናትህ አማጠችህ።
6 ፤ እንደ ማኅተም በልብህ፥ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና፥ ቅንዓትም እንደ ሲኦል የጨከነች ናትና። ፍንጣሪዋ እንደ እሳት ፍንጣሪ፥ እንደ እግዚአብሔር ነበልባል ነው።
7 ፤ ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም፥ ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይንቁታል።
8 ፤ እኛ ጡት የሌላት ታናሽ እኅት አለችን፤ ስለ እርስዋ በሚናገሩባት ቀን ለእኅታችን ምን እናድርግላት?
9 ፤ እርስዋ ቅጥር ብትሆን የብር ግንብ በላይዋ እንሠራለን፤ ደጅም ብትሆን በዝግባ ሳንቃ እንከብባታለን።
10 ፤ እኔ ቅጥር ነኝ ጡቶቼም እንደ ግንብ ናቸው፤ በዚያን ጊዜ በፊቱ ሰላምን እንደምታገኝ ሆንሁ።
11 ፤ ለሰሎሞን በብኤላሞን የወይን ቦታ ነበረው፤ የወይኑን ቦታ ለጠባቂዎች አከራየው፤ ሰው ሁሉ ለፍሬው ሺህ ብር ያመጣለት ነበር።
12 ፤ ለእኔ ያለኝ የወይን ቦታ በፊቴ ነው፤ ሰሎሞን ሆይ፥ ሺሁ ለአንተ፥ ሁለት መቶውም ፍሬውን ለሚጠብቁ ይሆናል።
13 ፤ በገነቱ የምትቀመጪ ሆይ፥ ባልንጀሮች የአንቺን ቃል ያደምጣሉ፤ ቃልሽን አሰሚኝ።
14 ፤ ውዴ ሆይ፥ ፍጠን፤ በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ምሰል።