መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን

1 2 3 4 5 6 7 8


ምዕራፍ 5

እኅቴ ሙሽራዬ ሆይ፥ ወደ ገነቴ ገባሁ፥ ከርቤዬን ከሽቱዬ ጋር ለቀምሁ፥ እንጀራዬን ከማሬ ጋር በላሁ፥ የወይን ጠጄን ከወተቴ ጋር ጠጣሁ። ባልንጀሮቼ ሆይ፥ ብሉ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ጠጪ፤ እስክትረኪ ድረስ ጠጪ።
2 ፤ እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል፤ የውዴ ቃል ነው፥ እርሱም ደጁን ይመታል፤ እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ ሆይ፥ በራሴ ጠል፥ በቈንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈችልኝ።
3 ፤ ቀሚሴን አወለቅሁ፤ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ፤ እንዴት አሳድፈዋለሁ?
4 ፤ ውዴ እጁን በቀዳዳ ሰደደ፥ አንጀቴም ስለ እርሱ ታወከ።
5 ፤ ለውዴ እከፍትለት ዘንድ ተነሣሁ፤ እጆቼ በደጅ መወርወሪያ ላይ ከርቤን አፈሰሱ፥ ጣቶቼ ፈሳሹን ከርቤ አንጠበጠቡ።
6 ፤ ለውዴ ከፈትሁለት፥ ውዴ ግን ፈቀቅ ብሎ አልፎ ነበር። ነፍሴ ከቃሉ የተነሣ ደነገጠች፤ ፈለግሁት፥ አላገኘሁትም፤ ጠራሁት፥ አልመለሰልኝም።
7 ፤ ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ መቱኝ፥ አቈሰሉኝም፤ ቅጥር ጠባቂዎችም የዓይነ ርግብ መሸፈኛዬን ወሰዱት።
8 ፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ አምላችኋለሁ፤ ውዴን ያገኛችሁት እንደ ሆነ፥ እኔ ከፍቅር የተነሣ መታመሜን ንገሩት።
9 ፤ አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድሽ ማን ነው? ይህን የሚያህል አምለሽናልና ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድሽ ማን ነው?
10 ፤ ውዴ ነጭና ቀይ ነው፥ ከእልፍ የተመረጠ ነው።
11 ፤ ራሱ ምዝምዝ ወርቅ ነው፤ ቈንዳላው የተዝረፈረፈ ነው፥ እንደ ቁራ ጥቁረትም ጥቁር ነው።
12 ፤ ዓይኖቹ በሙሉ ፈሳሽ አጠገብ እንዳሉ በወተት እንደ ታጠቡ በፈሳሽ ውኃ አጠገብ እንደ ተቀመጡ እንደ ርግቦች ናቸው።
13 ፤ ጕንጩና ጕንጩ የሽቱ መደብ እርከን እንዳለበት እንደ ሽቱ አትክልት ናቸው፤ ከንፈሮቹ እንደ አበቦች ናቸው፥ የሚፈስስ ከርቤንም ያንጠበጥባሉ።
14 ፤ እጆቹ የቢረሌ ፈርጥ እንዳለበት እንደ ወርቅ ቀለበት ናቸው፤ አካሉ ብልሃተኛ እንደ ሠራው በሰንፔር እንዳጌጠ እንደ ዝሆን ጥርስ ነው።
15 ፤ እግሮቹ በምዝምዝ ወርቅ እንደ ተመሠረቱ እንደ ዕብነ በረድ ምሰሶች ናቸው፤ መልኩ እንደ ሊባኖስና እንደ ዝግባ ዛፍ መልካም ነው።
16 ፤ አፉ እጅግ ጣፋጭ ነው፥ እርሱም ፈጽሞ ያማረ ነው፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ ውዴ ይህ ነው፥ ባልንጀራዬም ይህ ነው።