መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን

1 2 3 4 5 6 7 8


ምዕራፍ 7

አንቺ ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ፤ እናይሽ ዘንድ ተመለሽ፥ ተመለሽ። በሱላማጢስ ምን ታያላችሁ? እርስዋ እንደ መሃናይም ዘፈን ናት።
2 ፤ አንቺ የመኰንን ልጅ ሆይ፥ እግሮችሽ በጫማ ውስጥ እንዴት ውቦች ናቸው! ዳሌዎችሽስ በአንጥረኛ እጅ እንደ ተሠሩ እንደ ዕንቍዎች ይመስላሉ።
3 ፤ እንብርትሽ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበት እንደ ተነጠጠ ጽዋ ነው፤ ሆድሽ እንደ ስንዴ ክምር፥ በአበባም እንደ ታጠረ ነው።
4 ፤ ሁለቱ ጡቶችሽ እንደ ሁለቱ መንታ እንደ ሚዳቋ ግለገሎች ናቸው።
5 ፤ አንገትሽ እንደ ዝሆን ጥርስ ግንብ ነው፤ ዓይኖችሽ በሐሴቦን ውስጥ በባትረቢ በር አጠገብ እንደ ውኃ ኵሬዎች ናቸው፤ አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አፋዛዥ እንደሚመለከት እንደ ሊባኖስ ግንብ ነው።
6 ፤ ራስሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ በላይሽ ነው፤ የራስሽም ጠጕር እንደ ሐምራዊ ሐር ነው፤ ንጉሡ በሹርባው ታስሮአል።
7 ፤ ወዳጄ ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ!
8 ፤ ይህ ቁመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም የወይን ዘለላ ይመስላሉ።
9 ፤ ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ ጫፎችዋንም እይዛለሁ አልሁ፤ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ የአፍንጫሽም ሽቱ እንደ እንኮይ ናቸው።
10 ፤ ጕሮሮሽ ለወዳጄ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥ የተኙትን ከንፈሮች ይናገሩ ዘንድ እንደሚያደርግ፥ እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው።
11 ፤ እኔ የውዴ ነኝ፥ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው።
12 ፤ ውዴ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ በመንደሮችም እንደር።
13 ፤ ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፤ ወይኑ አብቦ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እንይ፤ በዚያ ውዴን እሰጥሃለሁ።
[14]፤ ትርንጎዎች መዓዛን ሰጡ፤ መልካሞች ፍሬዎች ሁሉ፥ አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ፤ ውዴ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ።