መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25


ምዕራፍ 17

በይሁዳ ንጉሥ በአካዝ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ንጉሥ ሆነ፤ ዘጠኝ ዓመትም ነገሠ።
2 ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ነገር ግን ከእርሱ አስቀድሞ እንደ ነበሩት እንደ እስራኤል ነገሥታት አይደለም።
3 ፤ የአሦርም ንጉሥ ስልምናሶር በእርሱ ላይ ወጣ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፥ ግብርም አመጣለት።
4 ፤ የአሦርም ንጉሥ በሆሴዕ ላይ ዓመፅ አገኘ፤ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ንጉሥ ወደ ሴጎር ልኮ ነበርና፤ እንደ ልማዱም በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ግብር አልሰጠምና፤ ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ይዞ በወህኒ ቤት አሰረው።
5 ፤ የአሦርም ንጉሥ በምድር ሁሉ ላይ ወጣ፥ ወደ ሰማርያም ወጥቶ ሦስት ዓመት ከበባት።
6 ፤ በሆሴዕ በዘጠኝኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ወሰደ፥ እስራኤልንም ወደ አሦር አፈለሰ፥ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው።
7 ፤ የእስራኤልም ልጆች ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ፥ ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በድለው ነበርና፥ ሌሎችንም አማልክት አምልከው ነበርና፥
8 ፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ባሳደዳቸው በአሕዛብ ሥርዓት፥ የእስራኤልም ነገሥታት ባደረጓት ሥርዓት ሄደው ነበርና እንደዚህ ሆነ።
9 ፤ የእስራኤልም ልጆች በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ቅን ያልሆነን ንገር በስውር አደረጉ፤ በከተሞቻቸውም ሁሉ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ተመሸገች ከተማ ድረስ በከፍታዎቹ ላይ መስገጃዎችን ሠሩ።
10 ፤ በረጃጅሙ ኮረብታ ሁሉ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ ታች ሐውልቶችንና የማምለኪያ ዐፀዶችን ተከሉ፤
11 ፤ እግዚአብሔርም ከፊታቸው ያወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉት፥ በኮረብቶቹ መስገጃዎች ሁሉ ላይ ያጥኑ ነበር፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ ክፉ ነገር አደረጉ፤
12 ፤ እግዚአብሔርም የከለከላቸውን ጣዖቶች አመለኩ።
13 ፤ እግዚአብሔርም። ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለአባቶቻችሁም እንዳዘዝሁት፥ ባባሪያዎቼ በነቢያት የላክሁላችሁን ትእዛዜንና ሥርዓቴን ሕጌንም ሁሉ ጠብቁ ብሎ በነቢዩ ሁሉና በባለ ራእዩ አፍ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ መሰከረ።
14 ፤ ነገር ግን አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዳላመኑ እንደ አባቶቻቸው አንገት አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙም።
15 ፤ ሥርዓቱንም ከአባቶቻቸውም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን፥ ያጸናላቸውንም ምስክሩን ናቁ፤ ከንቱ ነገርንም ተከተሉ፥ ምናምንቴዎችም ሆኑ፥ እግዚአብሔርም እንደ እነርሱ እንዳይሠሩ ያዘዛቸውን በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብን ተከተሉ።
16 ፤ የአምላካቸውንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ተዉ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም የሁለቱን እንቦሶች ምስሎች አደረጉ፥ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከሉ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገዱ፥ በኣልንም አመለኩ።
17 ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አሳለፉአቸው፥ ምዋርተኞችና አስማተኞችም ሆኑ፥ ያስቈጡትም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ።
18 ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፥ ከፊቱም ጣላቸው፤ ከይሁዳም ነገድ ብቻ በቀር ማንም አልቀረም።
19 ፤ ይሁዳም ደግሞ እስራኤል ባደረጋት ሥርዓት ሄደ እንጂ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም።
20 ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ዘር ሁሉ ጠላ፥ አስጨነቃቸውም፥ ከፊቱም እስኪጥላቸው ድረስ በበዝባዦች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
21 ፤ እስራኤልንም ከዳዊት ቤት ለየ፤ የናባጥንም ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን ከመከተል እስራኤልን መለሰ፥ ታላቅም ኃጢአት አሠራቸው።
22 ፤ የእስራኤልም ልጆች ኢዮርብዓም ባደረገው ኃጢአት ሁሉ ሄዱ፤
23 ፤ እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያቱ ሁሉ አፍ እንደ ተናገረው እስራኤልን ከፊቱ እስኪያወጣ ድረስ ከእርስዋ አልራቁም። እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከምድሩ ወደ አሦር ፈለሰ።
24 ፤ የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ ከአዋና ከሐማት ከሴፈርዋይም ሰዎችን አመጣ፥ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ።
25 ፤ በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶች ሰደደባቸው፥ ይገድሉአቸውም ነበር።
26 ፤ ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ። ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁም፤ የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፥ እነሆም፥ ገደሉአቸው ብለው ተናገሩት።
27 ፤ የአሦርም ንጉሥ። ከዚያ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፥ የአገሩንም አምላክ ወግ ያስተምራቸው ብሎ አዘዘ።
28 ፤ ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱ መጥቶ በቤቴል ተቀመጠ፥ እግዚአብሔርንም እንዴት እንዲፈሩት ያስተምራቸው ነበር።
29 ፤ በየሕዝባቸውም አምላካቸውን አደረጉ፥ ሰምራውያንም በሠሩት በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩበት ከተሞቻቸው አኖሩአቸው።
30 ፤ የባቢሎንም ሰዎች ሱኮትበኖትን ሠሩ፤ የኩታም ሰዎች ኤርጌልን ሠሩ፤
31 ፤ የሐማትም ሰዎች አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅን ሠሩ፤ የሴፈርዋይም ሰዎችም ለሴፈርዋይም አማልክት ለአድራሜሌክና ለአነሜሌክ ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ነበር።
32 ፤ እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፥ ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናት አደረጉ፥ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር።
33 ፤ እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር።
34 ፤ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ቀደመው ልማድ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም፥ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዓትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም አያደርጉም።
35 ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። ሌሎችን አማልክት አትፍሩ፥ አትስገዱላቸው፥ አታምልኩአቸው፥ አትሠዉላቸው፤
36 ፤ ነገር ግን በታላቅ ኃይል በተዘረጋችም ክንድ ከግብጽ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔር እርሱን ፍሩ፥ ለእርሱም ስገዱ፥ ለእርሱም ሠዉ፤
37 ፤ የጻፈላችሁንም ሥርዓትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም ለዘላለም ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ።
38 ፤ ከእናንተም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ።
39 ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እርሱም ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ ያድናችኋል።
40 ፤ ነገር ግን እንደ ቀደመው ልማዳቸው አደረጉ እንጂ አልሰሙም።
41 ፤ እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር፤ ልጆቻቸውም የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው እንዳደረጉ እንዲሁ እስከ ዛሬ ድረስ ያደርጋሉ።