ምዕራፍ 2

እንዲህም ሆነ፤ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ሊያወጣው በወደደ ጊዜ ኤልያስ ከኤልሳዕ ጋር ከጌልገላ ተነሣ።
2 ፤ ኤልያስም ኤልሳዕን። እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚህ ቆይ አለው። ኤልሳዕም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ወደ ቤቴልም ወረዱ።
3 ፤ በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ወጥተው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ አላቸው።
4 ፤ ኤልያስም። ኤልሳዕ ሆይ፥ እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ።
5 ፤ ወደ ኢያሪኮም መጡ። በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ ብሎ መለሰ።
6 ፤ ኤልያስም። እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ሁለቱም ሄዱ።
7 ፤ ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፥ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር።
8 ፤ ኤልያስም መጐናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው፥ ውኃውንም መታ፥ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ።
9 ፤ ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን። ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን አለው፤ ኤልሳዕም። መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።
10 ፤ እርሱም። አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም አለ።
11 ፤ ሲሄዱም። እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።
12 ፤ ኤልሳዕም አይቶ። አባቴ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች፥ ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ከሁለት ተረተረው።
13 ፤ ከኤልያስም የወደቀውን መጐናጸፊያ አነሣ፥ ተመልሶም በዮርዳኖስ ዳር ቆመ።
14 ፤ ከኤልያስም የወደቀውን መጎናጸፊያ ወስዶ ውኃውን መታና። የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው? አለ፤ ውኃውንም በመታ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ።
15 ፤ ከኢያሪኮም መጥተው በአንጻሩ የነበሩት የነቢያት ልጆች ባዩት ጊዜ። የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል አሉ። ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ ወደ ምድር ተደፉ።
16 ፤ እነርሱም። እነሆ፥ ከባሪያዎችህ ጋር አምሳ ኃያላን ሰዎች አሉ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደ አንድ ተራራ ወይም ወደ አንድ ሸለቆ ጥሎት እንደ ሆነ፥ ሄደው ጌታህን ይፈልጉት ዘንድ እንለምንሃለን አሉት። እርሱም። አትስደዱ አላቸው።
17 ፤ እስኪያፍርም ድረስ ግድ ባሉት ጊዜ። ስደዱ አለ፤ አምሳም ሰዎች ሰደዱ፤ ሦስት ቀንም ፈልገው አላገኙትም።
18 ፤ በኢያሪኮም ተቀምጦ ሳለ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም። አትሂዱ አላልኋችሁምን? አላቸው።
19 ፤ የከተማይቱም ሰዎች ኤልሳዕን። እነሆ፥ ጌታችን እንደምታይ የዚች ከተማ ኑሮ መልካም ነው፤ ውኃው ግን ክፉ ነው፥ ምድሪቱም ፍሬዋን ትጨነግፋለች አሉት።
20 ፤ እርሱም። አዲስ ማሰሮ አምጡልኝ፥ ጨውም ጨምሩበት አለ፤ ያንንም አመጡለት።
21 ፤ ውኃው ወዳለበቱም ምንጭ ወጥቶ ጨው ጣለበትና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ውኃ ፈውሼዋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ሞትና ጭንገፋ አይሆንበትም አለ።
22 ፤ ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ነገር ውኃው እስከ ዛሬ ድረስ ተፈውሶአል።
23 ፤ ከዚያም ወደ ቤቴል ወጣ፤ በመንገድም ሲወጣ ብላቴኖች ከከተማይቱ ወጥተው። አንተ መላጣ፥ ውጣ፤ አንተ መላጣ፥ ውጣ ብለው አፌዙበት።
24 ፤ ዘወርም ብሎ አያቸው፥ በእግዚአብሔርም ስም ረገማቸው፤ ከዱርም ሁለት ድቦች ወጥተው ከብላቴኖች አርባ ሁለቱን ሰባበሩአቸው።
25 ፤ ከዚያም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደ፥ ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።