መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25


ምዕራፍ 20

በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስከ ሞት ድረስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል አለው።
2 ፤ ፊቱንም ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
3 ፤ አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፥ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ። ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ።
4 ፤ ኢሳይያስም ወደ መካከለኛው ከተማ አደባባይ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት።
5 ፤ ተመልሰህ የሕዝቤን አለቃ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ እፈውስሃለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ትወጣለህ።
6 ፤ በዕድሜህም ላይ አሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ፤ አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ስለ እኔም ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ።
7 ፤ ኢሳይስም፥ የበለስ ጥፍጥፍ አምጡልኝ አለ፤ አምጥተውም በእባጩ ላይ አደርጉለት፥ እርሱም ተፈወሰ።
8 ፤ ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፥ እግዚአብሔር እንዲፈውሰኝ፥ እኔስ በሦስተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንድወጣ ምልክቱ ምንድር ነው? አለው።
9 ፤ ኢሳይያስም፥ እግዚአብሔር የተናገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል፤ ጥላው አሥር ደረጃ ወደ ፊት ይሄድ ዘንድ ወይም አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ ዘንድ ትወድዳለህን? አለ።
10 ፤ ሕዝቅያስም፥ ጥላው አሥር ደረጃ ቢጨምር ቀላል ነገር ነው፤ እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ጥላው አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ አለው።
11 ፤ ነቢዩም ኢሳይያስ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ ጥላውንም በአካዝ የጥላ ስፍራ ሰዓት ላይ በወረደበት መንገድ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ መለሰው።
12 ፤ በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን ሕዝቅያስ እንደ ታመመ ሰምቶ ነበርና ደብዳቤና እጅ መንሻ ወደ ሕዝቅያስ ላከ።
13 ፤ ሕዝቅያስም ደስ አለው፥ ግምጃ ቤቱንም ሁሉ፥ ብሩንና ወርቁንም፥ ቅመሙንና የከበረውንም ዘይት፥ መሣሪያም ያለበትን ቤት በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው በቤቱና በግዛቱ ሁሉ ካለው ሕዝቅያስ ያላሳያቸው የለም።
14 ፤ ነቢዩም ኢሳያሳ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ መጥቶ። እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? ከወዴትስ መጡልህ? አለው። ሕዝቅያስም። ከሩቅ አገር ከባቢሎን መጡ አለው።
15 ፤ እርሱም። በቤትህ ያዩት ምንድር ነው? አለው፤ ሕዝቅያስም። በቤቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በቤተ መዛግብቴ ካለው ያላሳየኋቸው የለም አለው።
16 ፤ ኢሳይያስም ሕዝቅያስን። የእግዚአብሔርን ቃል ስማ።
17 ፤ እነሆ፥ በቤትህ ያለው ሁሉ፥ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል፤ ምንም አይቀርም፥ ይላል እግዚአብሔር።
18 ፤ ከአንተም ከሚወጡት ከምትወልዳቸው ልጆችህ ማርከው ይወስዳሉ፤ በባቢሎንም ንጉሥ ቤት ውስጥ ጃንደረቦች ይሆናሉ አለው።
19 ፤ ሕዝቅያስም ኢሳይያስን። የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው አለው። ደግሞም። በዘመኔ ሰላምና እውነት የሆነ እንደ ሆነ መልካም አይደለምን? አለ።
20 ፤ የቀረውም የሕዝቅያስ ነገር፥ ጭከናውም ሁሉ፥ ኵሬውንና መስኖውንም እንደ ሠራ፥ ውኃውንም ወደ ከተማይቱ እንዳመጣ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
21 ፤ ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።