ምዕራፍ 1

በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው የአሞጽ ልጅ የኢሳይያስ ራእይ።
2 ፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፥ ምድርም አድምጪ፤ ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም፥ እነርሱም አመጹብኝ።
3 ፤ በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም፥ ሕዝቤም አላስተዋለም።
4 ፤ ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ፥ የክፉዎች ዘር፥ ርኵሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል የእስራኤልንም ቅዱስ አቃልለዋል ወደ ኋላቸውም እየሄዱ ተለይተዋል።
5 ፤ ደግሞስ ዓመፃ እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሰፋላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል።
6 ፤ ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም።
7 ፤ ምድራችሁ ባድማ ናት፤ ከተሞቻችሁ በእሳት ተቃጠሉ፤ እርሻችሁንም በፊታችሁ ሌሎች ይበሉታል፤ ባዕድ እንዳፈረሳት ምድር ባድማ ሆነች።
8 ፤ የጽዮንም ሴት ልጅ በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ፥ በዱባ አትክልትም እንዳለ ጎጆ፥ እንደተከበበችም ከተማ ሆና ቀረች።
9 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር።
10 ፤ እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ።
11 ፤ የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም።
12 ፤ በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው?
13 ፤ ምናምንቴውን ቍርባን ጨምራችሁ አታምጡ፤ ዕጣን በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፤ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም፤ በደልንም የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም።
14 ፤ መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ።
15 ፤ እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል።
16 ፤ ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፥
17 ፤ መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ።
18 ፤ ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች።
19 ፤ እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤
20 ፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።
21 ፤ ፍርድ ሞልቶባት የነበረው የታመነችይቱ ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ አድሮባት ነበር፥ አሁን ግን ገዳዮች አሉባት።
22 ፤ ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፤ የወይን ጠጅሽ ከውሃ ጋር ተደባለቀ።
23 ፤ አለቆችሽ አመጸኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፤ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፥ ዋጋም ለማግኘት ይሮጣሉ፤ ለድሀ አደጉ አይፈርዱም፥ የመበለቲቱም ሙግት ወደ እነርሱ አይደርስም።
24 ፤ ስለዚህ የእስራኤል ኃያል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በጠላቶቼ ላይ ቍጣዬን እፈጽማለሁ፥ የሚቋቋሙኝንም እበቀላለሁ።
25 ፤ እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፥ ዝገትሽንም በጣም አነጻለሁ፥ ቆርቆሮሽንም ሁሉ አወጣለሁ፤
26 ፤ ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያው ጊዜ መልሼ አስነሣለሁ፤ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ የታመነችም ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።
27 ፤ ጽዮን በፍርድ ከእርሷም የሚመለሱ በጽድቅ ይድናሉ።
28 ፤ በደለኞችና ኃጢአተኞች ግን በአንድነት ይሰበራሉ፥ እግዚአብሔርንም የሚተዉ ይጠፋሉ።
29 ፤ በወደዳችኋት የአድባር ዛፍ ታፍራላችሁና፥ ስለ መረጣችኋትም አትክልት እፍረት ይይዛችኋልና፤
30 ፤ ቅጠልዋ እንደ ረገፈ ዛፍ፥ ውሃም እንደሌለባት አትክልት ትሆናላችሁና።
31 ፤ ኃይለኛውም እንደ ተልባ ጭረት፥ ሥራውም እንደ ጠለሸት ይሆናል፤ አብረውም ይቃጠላሉ እነርሱንም የሚያጠፋ የለም።